ኢትዮጵያና ሱዳን በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና ዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፎች በትብብር ለመሥራት ተስማሙ።

21
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ እና የሱዳን መንግሥታት በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂና ቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፎች በትብብር መሥራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ እና የሱዳን ሪፐብሊክ የቴሌኮሙኒኬሽን እና ዲጂታል ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር አደል ሐሰን መሐመድ ተፈራርመውታል፡፡
ዶክተር በለጠ ሞላ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ እና ሱዳን እህትማማችና የረጅም ጊዜ የጋራ ታሪክ ያላቸው ሀገራት መኾናቸውን አውስተዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች የጋራ ታሪክ፣ የጋራ ድንበር የሚጋሩና የአንድ ወንዝ ልጆች መኾናቸውን ጠቅሰው ፤ በሳይንስ ቴክኖሎጂና በኮሙኒኬሽን ዘርፍ ተባብረው ለመስራት መነሳሳታቸው ተገቢና ወቅታዊ ነው ብለዋል፡፡
ሀገራቱን ዘመኑ በሚጠይቀው የቴሌኮሙኒኬሽን፣ ኢንፎርሜሽንና ዲጂታል ቴክኖሎጂ በማስተሳሰር የህዝቦቹን ኑሮ ማሻሻል ከመንግሥታት እና ከዚህ ትውልድ ይጠበቃልም ነው ያሉት፡፡
ስምምነቱን ወደ ተግባር የሚቀይሩና በዘርፉ ውጤት የሚያመጡ እቅዶች ተነድፈው እንዲተገበሩ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል፡፡
አደል ሐሰን መሐመድ በበኩላቸው፤ ልዑኩ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በቴሌኮምና ዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ በትብብር ለመስራትና ዲጂታል ኢኮኖሚን በጋራ ለመዘርጋት የሚያስችል ስምምነት ለመፈራረም መኾኑን ገልጸዋል።
በቀጣይ የቴክኒክ ቡድን ተቋቁሞ ስምምነቱን ለመተግበር እንደሚሰራም ገልጸዋል።
በሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የተፈረመው የሁለትዮሽ ስምምነት በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል።
በቀጣይ የስምምነቱን አፈጻጸም የሚከታተልና የሚያስፈጽም የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ በጋራ ተቋቁሞ ወደ ሥራ እንደሚገባ መግለጹን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!