“አፍሪካ ከድህነት ለመውጣት ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋታል” የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ፔድሮ

28
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ
ባሕር ዳር:መጋቢት 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አፍሪካ ከድህነት ለመውጣት ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋታል ሲሉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ፔድሮ ተናገሩ።
55ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የፍይናንስ፣ ፕላኒንግና ምጣኔ ሀብት ልማት የሚኒስትሮች ጉባኤ የሙያተኞች ኮሚቴ ዛሬ በአዲስ አበባ መካሔድ ጀምሯል።
በጉባኤው በክፈቻ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ፔድሮ በአፍሪካ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በከፋ ድህነት ውስጥ እንደሚገኙ አንስተዋል።
ለዚህም የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያቶችን በመጥቀስ በዓለም አቀፉ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት 62ሚሊዮን ሰዎች በአንድ ዓመት ብቻ ወደ ድህነት መግባታቸውን አንስተዋል።
በአጠቃላይ በአፍሪካ 695ሚሊዮን ሰዎች በድህነት ወይንም ወደ ድህነት ለመግባት ችግር ውስጥ ያሉ መሆናቸውን በመጥቀስ ይህም ከአህጉሩ አጠቃላይ ሕዝብ 50 በመቶ እንደሆነ አክለዋል።
ከእዚህ ውስጥ በተለይም ሕጻናትና ሴቶች በተለየ መልኩ ተጋላጭ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም በአህጉሪቱ ያለውን ሀብት በመጠቀም ከድህነት ለመውጣት ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት ወሳኝ በመሆኑ ፖሊሲ አውጪዎችና ሙያተኞች ድህነትን መቋቋም የሚችልና ቀጣይነት ያለው ምጣኔ ሀብትን ለመገንባት በትኩረት መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።
May be an image of 3 people, people standing and indoorለችግርና አደጋ ጊዜ ምላሽ መስጠት የሚያስችልና ቀጣይነት ያለው የፍይናንስ አቅምን መገንባት፣ መሰረተ ልማትን ማጠናከር፣ የሰው ሀይል አቅም ግንባታ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በአጀንዳ 2063 የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ከድህነት ለመውጣት በአፍሪካ የሚተገበሩ ልማቶችን አጋር አካላት በፋይናንስ መደገፍ፣ ቀጣይነት ያለው የኢንዱስትሪ ልማት ላይ ማተኮር፣ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ እና ሌሎች አማራጮችን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።
የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ነመራ ገበየሁ በበኩላቸው የድህነት መጨመርና የእኩልነት እጦት በአፍሪካ ውሰጥ ተጠቃሽ ችግሮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም የበለጸገችና ለዜጎች ምቹ አህጉርን ለመፍጠር ትብብርን ማጠናከር፣ ከልማት አጋር ድርጅቶች ጋር መስራት፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀብትን ማንቀሳቀስ፣ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥ ለአፍሪካ አማራጭ የፋይናንስ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።
ዛሬ በተጀመረው የሙያተኞች ስብሰባ ከተባበሩት መንግሥታት፣ ከልማት አጋሮች፣ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮችና የሚመለከታቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!