አዳዲስ ዝርያዎችን በማባዛት የአርሶ አደሮችን ምርታማነት ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት አስታወቀ፡፡

0
49
አዳዲስ ዝርያዎችን በማባዛት የአርሶ አደሮችን ምርታማነት ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 07/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር ጥላዬ ተክለወልድ (ዶክተር) ኢንስትቲዩቱ የአርሶ አደሮችን ምርታማነት ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ሥራውን ከግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር እየሠሩት መኾኑንም ነው የገለጹት፡፡ ዶክተር ጥላዬ የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ቴክኖሎጅዎችን ማፍለቅ፣ የፈለቁ ቴክኖሎጅዎችን የመነሻ ዘር ማባዛት እና የተባዙ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ የሚተዋወቅበትን ሁኔታ ማመቻቸት ዋና ዋና ተግባራት መኾናቸውን አስረድተዋል፡፡
ዳይሬክተሩ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች እና ዩኒቨርስቲዎችን በማቀናጀት ውጤታማ የምርምር ሥራዎችን እንዲያከናውኑ እገዛ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ በክልሉ የግብርና ምርምር የአቅም ግንባታ ሥራን በሠፊው እየሠሩ መኾኑንም ነግረውናል፡፡ ኢንስትቲዩቱ በሽታን እና ድርቅን መቋቋም የሚችሉ፣ ምርታማነትን የሚያሻሽሉ፣ በምርምር የተገኙ እና ለግብርና ተግዳሮት መፍትሔ የሚሠጡ ዝርያዎችን አባዝቶ ለዘር አባዥዎች እያቀረበ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጅ ዝርያዎችን የማስተዋወቅ ሥራው ዝቅተኛ እንደኾነ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት “ኒውኩለስ” የተባለውን ዘር ከውጭ በማስመጣት አራቢ ዘር፣ ቅድመ መሥራች ዘር እና መሥራች ዘር በማባዛት ለዘር አራቢዎች፣ ለማኅበራት እና ለዩኔየኖች በማቅረብ ዘሩ ተባዝቶ ለአርሶ አደሮች እንዲዳረስ እየሠራ መኾኑንም አስረድተዋል፡፡ አንድ ዘር በብዛት ተመርቶ አርሶ አደሮች መንደር ከመድረሱ በፊት የተመረጠው ዘር ጥራቱ የተረጋገጠ፣ ድርቅን መቋቋም የሚችል፣ ለየትኛው አካባቢ ተስማሚ እንደኾነ በተደጋጋሚ ተፈትሾ እንደሚቀርብም ተናግረዋል፡፡
የአርሶ አደሮችን ፍላጎት መሠረት ተደርጎ ከዘር አባዥዎች ጋር ውል እንደሚያዝም ነግረውናል፡፡ ኢንስትቲዩቱ አራቢ ዘርን በተሻለ መጠን እያመረተ ሲኾን ቅድመ መስራች ዘር እና መስራች ዘር በቦታ እጥረት እና በማሽን ችግር የሚፈለገውን ያህል ማምረት አለመቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
ዘር የማባዛት ሥራው በአርሶ አደሮች ማሳ፣ በባለሀብቶች መሬት እና በማኅበራት ማሳዎች ላይ እየተሠራ ነው፡፡ ኢንስትቲዩቱ የአማራ ክልል ከሚያስፈልገው አራቢ ዘር፣ ቅድመ መስራች ዘር እና መስራች ዘር ውስጥ 70 በመቶ ያህሉን እንደሚሸፍን አስረድተዋል፡፡ ዳይሬክተሩ እንዳሉት እስካሁን የተለያዬ ዝርያ ያላቸው አንድ ሺህ ሰባት መቶ ኩንታል አራቢ ዘር፣ ቅድመ መስራች ዘር እና መስራች ዘር በኢንስትቲዩቱ ተባዝቷል፡፡ የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት በየዓመቱ አዳዲስ ዝርያዎችን በምርምር ማዕከላት ቢያወጣም የማስተዋወቅ ሥራው ዝቅተኛ በመኾኑ አርሶ አደሮች መንደር ደርሶ ሕይወታቸውን እየቀየረው አለመኾኑን ገልጸዋል፡፡
በኢንስትቲዩቱ በቆሎ፣ ጤፍ እና ስንዴ በብዛት የሚራቡ አዝዕርቶች ይሁኑ እንጅ ባቄላ፣ ማሽላ፣ ሠሊጥ፣ ድንች እና የመሳሰሉ አዝዕርቶችንም አራቢ ዘር፣ ቅድመ መስራች ዘር እና መስራች ዘር እያመረተ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ የመሬት እና የማሽነሪ እጥረት መኖር፣ የማስተዋወቅ ሥራው ዝቅተኛ መኾንና በበቂ መጠን ዘር አባዝቶ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ዋነኛ እንቅፋቶች መኾናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት እ.አ.አ እስከ 2017 ድረስ 42 ዓይነት የጤፍ ዝርያ፣ 80 ዓይነት የዳቦ ስንዴ ዝርያ፣ 39 ዓይነት የመኮረኒ ስንዴ ዝርያ፣ 70 ዓይነት የበቆሎ ዝርያ፣ 51 ዓይነት የማሽላ ዝርያዎችን በድምሩ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ዝርያዎችን አባዝቶ የለቀቀ ቢኾንም ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ ጥቂቶች ብቻ መኾናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ለዘር ብዜት እንዲውል በክልል ምክር ቤት የጸደቀው 23 ሺህ ሄክታር መሬት ጥቅም ላይ አለመዋሉን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚመለከተው አካል ኀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ከግብርና ምርምር ተቋም የሚወጡ ዝርያዎችን በማስተዋወቅ በኩል የግብርና ምርምር ማዕከላት፣ ግብርና ቢሮ እና ዩኒቨርሲቲዎች በሚሠሩት ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት አካተው በመሥራት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here