አዲስ የወጣው የመሬት ካሳ ዓዋጅ ደንብ እና መመሪያ ስላልተዘጋጀለት ደንበኞችን ለማስተናገድ መቸገሩን የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

1
11914

ከተማ አስተዳደሩ ከመኖሪያ ቤት፣ ከኢንቨስትመንት እና መሠረተ ልማትን ከማስፋፋት ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ጥያቄዎች ይነሱበታል፡፡ ይሁን እንጂ ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት አልቻለም፡፡ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ደጀኔ ተሾመ ለአብመድ እንደተናገሩት ከተማ አስተዳደሩ መሬትን ከሦስተኛ ወገን ነጻ ለማድረግ ገንዘብ አዘጋጅቶ እየጠበቀ ቢሆንም አዋጁ መመሪያና ደንብ ስላልተዘጋጀለት ተግባራዊ ማድረግ አልተቻለም፡፡ በመኖሪያ ቤት ከተደራጁ 1ሺህ 90 የተለያዩ የኅብረት ሥራ ማኅበራት መካከል 633 የሚሆኑት መስፈርቱን አሟልተው ቦታ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ብርሃኑ ገብረኢየሱስ እንዳሉት የከተማዋ የኢንቨስትመንት ፍሰት ከፍተኛ ጭማሪ የታየበት ነው፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት የኢንቨስትመንት ፍሰት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ጨምሯል፡፡ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው፣ ሰፊ የሥራ እድል የሚፈጥሩ እና ትላልቅ ካፒታል ያላቸው 83 ፕሮጀክቶች ጥያቄ ማቅረባቸውንም አቶ ብርሃኑ ነግረውናል፡፡

የኢንቨስትመንት ቦታ ጥያቄ ያቀረቡት እነዚህ ፕሮጀክቶች 9 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም መሬት ከሦስተኛ ወገን ነጻ አድርጎ ይጠብቅ የነበረው ከተማ አስተዳደሩ ካሳ መክፈል አልቻለም፡፡ ባለሀብቶች በራሳቸው ከፍለው ወደ ሥራ መግባት ቢፈልጉም መመሪያ እና ደንቡ ባለመዘጋጀቱ ምክንያት አለመቻላቸውን ነግረውናል፡፡

በሊዝ ውለታቸው መሠረት ፈጥነው ወደ ሥራ ያልገቡ ፕሮጀክቶችን አጥንቶ መሬትን ወደ መሬት ባንክ በማስገባት ለትክክለኛው አልሚ በማስተላለፍ ከተማ አስተዳደሩ ጊዜያዊ መፍትሔ እየሰጠ ነው፡፡ በስድስት ወራቱ የ30 ፕሮጀክቶችን መሬት በመንጠቅ እንዲሁም የወሰዱትን መሬት ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ሳያውሉ ከቀሩ ፕሮጀክቶች ላይ በመቀነስ ጥያቄ ካቀረቡ 83 ፕሮጀክቶች መካከል 30 ለሚሆኑት መፍትሔ መስጠት ችሏል፡፡ ይሁን እንጂ የተወሰደው የመፍትሔ አማራጭ ብቻውን ለከተማው የኢንቨስትመንት ጥያቄ ምላሽ እንዳልሰጠ አቶ ብርሃን ተናግረዋል፡፡

የመተማመኛ ደብዳቤ ለአርሶ አደሮች በመስጠት ለመደራደር ፍላጎት ቢኖርም አርሶ አደሮች ካሳ ሳይከፈላቸው ቦታቸውን ለመልቀቅ ፍቃደኛ አይደሉም ተብሏል፡፡ ከተማ አስተዳደሩም ጥያቄውን ለከልል ማቅረቡን ነው የተናገሩት፡፡ በመሆኑም የክልሉ መንግሥት ችግሩ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እያስነሳ በመሆኑ ምላሽ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡

የአማራ ክልል ገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ቢሮ በበኩሉ ጥያቄው ተገቢ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የቢሮው ምክትል ኃላፊ መለሰ ዳምጤ እንዳሉት መስከረም 12/2012 ዓ.ም የወጣው አዲስ የካሳ ክፍያ አዋጅ ቀደም ብሎ በዘርፉ ይነሳ ለነበረው ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነው፡፡ ከሦስት ወር ባልበለጠ ጊዜ ደግሞ የማስፈጸሚያ ደንብ መውጣት አለበት፡፡ ይህንን ተከትሎ ነው ክልሎች አዋጁን እና ደንቡን ተከትለው የራሳቸውን መመሪያ የሚያወጡት፡፡ ደንቡ በፌዴራል መንግሥት ደረጃ እየተዘጋጀ መሆኑን እና ከየክልሉ በተውጣጡ አካላት መተቸቱን ነግረውናል፡፡ መስተካከል የሚገባቸው ነገሮች ስለነበሩት እንደገና ተስተካክለው እንዲተቹ አቅጣጫ መሰጠቱንም አመላክተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በተፈጠረው መዘግየት ምክንያት ክልሉ የራሱን መመሪያ ማውጣት እንዳይችል አድርጎታል፡፡ የአማራ ክልል ገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ቢሮ አዋጁን መሠረት በማድረግ ረቂቅ መመሪያ ማዘጋጀቱንም አቶ መለሰ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ መለሰ ገለጻ ደንቡ እንደጸደቀ ረቂቅ አዋጁ ላይ ቀመር በማስገባት ወደ ሥራ የሚገባበ ይሆናል፡፡ የደንቡ መዘግየት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚከናወኑ የኢንቨስትመንት፣ የመሠረተ ልማት እና ሌሎች ተግባራት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ በመሆኑ የክልሉ መንግሥት ግፊት እያደረገ መሆኑንም ነው አቶ መለሰ የተናገሩት፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here