ባሕር ዳር: መጋቢት 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ እየተገነባ የሚገኘው አዲሱ የዓባይ ወንዝ ድልድይና መዳረሻ መንገዶች ግንባታ አፈጻጸም 94 በመቶ መድረሱን የፕሮጀክቱ ምክትል ተጠሪ መሃንዲስ ኢንጅነር ፍቅረሥላሴ ወርቁ ለአሚኮ ኦንላይን ሚዲያ ገልጸዋል።
የድልድዩ ዋና ዋና ሥራዎች በዕቅዱ መሰረት እየተከናወነ መኾኑን ነው የተናገሩት። አጠቃላይ የግንባታ ሂደቱም በመፋጠን ላይ ነው ብለዋል።
ግንባታው በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ከመንግሥት በተመደበ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ተበጅቶለት፣ በቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ ተቋራጭነት ነው እየተሠራ የሚገኘው። ድልድዩ 380 ሜትር ርዝመት ያለው ሲኾን የጎን ስፋቱም 43 ሜትር ነው። የዋናው ድልድይ መዳረሻ 4 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው መንገድ ግንባታም እየተከናወነ ነው።

በፕሮጀክቱ በርካታ ኢትዮጵያውያን የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሳተፉበት እንደኾነ የተናገሩት ኢንጂነር ፍቅረ ሥላሴ ወርቁ ፕሮጀክቱ የቴክኖሎጅ፣ የዕውቀት ሽግግርና በቂ ልምድም የሚወሰድበት ነው ብለዋል።
ግንባታው ጥራቱን ጠብቆ በተያዘለት በዚህ በጀት ዓመት ይጠናቀቃል ብለዋል ኢንጂነር ፍቅረ ሥላሴ።
የአሚኮ ኦንላይን ሚዲያ ሠራተኞችም አዲሱን የዓባይ ወንዝ ድልድይ ግንባታ በቦታው ተገኝተው ተመልክተዋል።
ድልድዩ ሲጠናቀቅ ለከተማዋ በትራንስፖርቱ ዘርፍ የትራፊክ መጨናነቅን ከመቅረፍ ባሻገር ሀገራዊ የኢኮኖሚ ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ እንደሆነ ተናግረዋል።
ድልድዩ የቱሪዝም መስብ መሆን የሚችልና በዘመናዊ ቴክኖሎጅ እየተገነባ የሚገኝ ትኩረት የተሰጠው ሀገራዊ ፕሮጀክት መኾኑን ተገንዝበናል ብለዋል። በከፍተኛ በጀት የሚገነቡ የልማት ፕሮጀክቶችን በቦታው ተገኝቶ መመልከትም ለቀጣይ የዘገባ ሥራ ግንዛቤ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!