“አዝጋሚ የሆነውን የግብርና ምርት እድገት ለመለወጥ ጉዞውን ከእርምጃ ወደ ሩጫ መቀየር ይገባል”ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ

0
121

ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አዝጋሚ የሆነውን የግብርና ምርት እድገት ለመለወጥ ጉዞውን ከእርምጃ ወደ ሩጫ መቀየር ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስገነዘቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አርሶ አደሩ ስንዴን ለፍጆታ ብቻ ሳይሆን ለገበያ ጭምር እንዲያመርት አቅሙን ማሳደግ ይገባል” ሲሉም ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራ የሚኒስትሮችና የክልል የርእሰ መስተዳደሮች የልኡካን ቡድን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምዕራብ ደምቢያ ወረዳ በበጋ መስኖ የለማ ስንዴና የጎርጎራ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክትን ጎብኝቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝቱ ላይ እንዳሉት አዝጋሚ የሆነውን የግብርና ምርት እድገት ለመለወጥ ጉዞውን ከእርምጃ ወደ ሩጫ መቀየር ይገባል።

በስንዴ ምርት ኢትዮጵያ ውስጥ አርሶ መብላት ብቻ ሳይሆን ጠግቦ መሸጥ የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

“ሰፊ የሚለማ መሬት፣ የሰው ጉልበትና እንዱሁም የተፈጥሮ ውኃ እያለን ከውጭ ሀገራት ስንዴ ሸማች መሆን ሊቀጥል አይገባም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፣ “አርሶ አደሩ የጀመረውን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት” አሳስበዋል።

በአማራ ክልል በዘንድሮው በጋ በመስኖ የለማውን 41 ሺህ ሄክታር መሬት በቀጣይ ዓመት ወደ150 ሺህ ሄክታር በማሳደግ ለሃገራዊ የስንዴ ልማት ግብ መሳካት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በልማቱ እየተሳተፉ ያሉ አርሶ አደሮችም የልማት ጀግና መሆናቸውን ያበረታቱት ጠቅላይ ሚነስትሩ፣ “በቀጣይ አስፈላጊውን የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችንና የግብርና ቴክኖሎጂዎች እንዲቀርቡ ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል” ብለዋል።

“ዘንድሮው በአማራ ክልል በበጋ መስኖ የለማው ስንዴ በቀጣይ ሰፋፊ እቅዶችን ማሳካት እንደሚቻል ማሳያ ነው” ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ናቸው።

አርሶ አደሩ፣ አመራሩና የግብርና ባለሙያው ለዕቅዱ መሳካት ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

“በቀጣይ ዓመት የኩታ ገጠም እርሻን በማስፋፋትና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የክልሉን የስንዴ ልማት እቅድ ለማሳደግ ከወዲሁ እንዘጋጅ” ብለዋል።

“ያየነው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እጅግ የሚደነቅና በክልሉ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አበረታች የልማት ሥራ መከናወኑን አመላካች ነው” ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ናቸው።

ጠንክሮ ከተሰራ የግብርናውን ዘርፍ እድገት በማሳለጥ ህዝብን ከምግብ ዋስትና ችግር ከማላቀቅ ባለፈ ለውጭ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶችን በአይነትም ሆነ በብዛት ማሳደግ እንደሚቻል አመልክተዋል።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ እርስቱ ይርዳው በበኩላቸው እንዳሉት ኢትዮጵያ በስንዴ ልመና የምትኖር ሳይሆን ከራሷ ተርፎ ለሌሎች የምትሸጥ ሀገር መሆን እንደምትችል በተግባር ማሳየት ይገባል ብለዋል። ዘገባው የኢዜአ ነው

“የመስክ ምልከታውና የልምድ ልውውጡ የበለጠ እንድንተጋ፣ሃገራችን ያላትን እምቅ ሃብት እንድናውቅና በትብብር ሀገር እንድንገነባ ትምህርት ይገኝበታል” ብለዋል።

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/