አንዲት ግራር – ቃልኪዳን የታሰረባት የነፃነት ተምሳሌት

0
211

ባሕር ዳር፡ ጥር 01/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጽናት የሚሰበክባት፣ አንድነት የሚጸናባት፣ ትብብር የሚጎመራባት፣ የአልደፈር ባይነት ወኔ የሚወረስባት ታሪካዊ ቦታ ነች፡፡

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የአርበኞች ማኅበር የተመሰረተባት ታሪካዊ የጀግንነታችን አሻራ ነች። በሰሜን ሸዋ ዞን ከሞጃና ወደራ ወረዳ መናገሻዋ ሰላድንጋይ ከተማ በቅርብ ርቀት አንቀላፊኝ ሜዳ በምትባል ስፍራ ትገኛለች፡፡ ‹‹አንዲት ግራር!›› ለረጅም ጊዜያት በአካባቢው ዛፍ በሌለበት 200 ዓመት ያስቆጠረች ብቸኛ የግራር ዛፍ ነበረች፡፡ ‹‹አንዲት ግራር›› የሚለው ስያሜ የተሰጣትም በዚሁ መነሻነት ነበር። የአካባቢው ነዋሪዎች እና የአስተዳደር ሰዎች እንደየ ዓላማቸው በዚች ግራር ጥላ ሥር ልዩ ልዩ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ተግባራትን ሲከውኑባት ነበር።

በ1888 ዓ.ም ጣልያን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመውረር በመጣች ጊዜ በአፄ ምኒልክ በሳል የአመራር ጥበብ አድዋ ላይ ሽንፈት መጎንጨቷ የሚታወቅ ነው። ታዲያ በዚህ ጦርነት የሸዋ አርበኞች የነበራቸው ሚና የጎላ እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል። የሸዋ አርበኞች የንጉሥ ምኒልክን የክተት አዋጅ ተቀብለው ወደ ጦር ሜዳው ከመጓዛቸው በፊት በየጭቃ ሹሞቻቸው አማካኝነት አንዲት ግራር ላይ ተገናኝተው ድል የሚያደርጉበትን የጦርነት ስልት መክረዋል፡፡ ለጠላት እጅ ላይሰጡም ተማምለዋል። ከመካከላቸው የሚሰዋ ቢኖር እንኳን ማንም የወገኑን አስከሬን ጥሎ እንዳይመለስ ቃል ኪዳን አስረዋል። የሆነው ሆኖ ጦርነቱን ኢትዮጵያ አሸነፈች።

ሽንፈቱን አምኖ መቀበል ያቃተው ፋሽስት ጣልያን ኢትዮጵያን ዳግም ለመውረር 40 ዓመታት ተዘጋጀ፡፡ በ1928 ዓ.ም ጦሩን አጠናክሮ ለሁለተኛ ጊዜ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት በግፍ ወረረ፡፡ የጣልያን ጦር በደንብ ተጠናክሮ ስለነበር በኢትዮጵያ በርካታ ግዛቶችን መቆጣጠር ቻለ፡፡ ሰሜናዊ የሀገሪቱን ክፍል ተቆጣጥሮ ሸዋ ላይ ወረራ ሊያደርግ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ጀመረ፡፡

ሀገራችን ስትደፈር ዝም ብለን አንመለከትም ያሉት የሸዋ አርበኞች የፋሽስት ጣልያን ጦርን መስቀሌ ገዳም ከምትባል አካባቢ ጦርነት ገጠሙት፡፡ በሐምሌ/1929 ዓ.ም የጣልያን ጦር የበላይነት ወስዶ ስለነበር አርበኞቹ ወራሪውን ድል ማድረግ የሚያስችል የጦርነት ስልት ለመቀየር ወሰኑ፡፡ በዱር በገደሉ ሠፍረው የነበሩት የጦር አለቆች ጥር 1/1931 ዓ.ም ጦራቸውን ይዘው በታሪካዊቷ አንዲት ግራር ተገናኙ፡፡ ከጦር አለቆቹ መካከል ራስ አበበ አረጋይ፣ ልጅ ግዛው ኃይሌ፣ ባላምባራስ ባሻህ ኃይሌ፣ ደጃዝማች ተሰማ እርገጤ፣ ፊታውራሪ ታደሰ በላይነህ፣ ልጅ ከፈለው ወልደፃድቅ፣ አቶ ፀሐይ እንቁፃዲቅ፣ አቶ ፀኃይ እንቁስላሴ፣ ራስ መስፍን ሽመልስ እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ በዚህ ቦታ ባላንባራስ ባሻህ ኃይሌ በመሩት ስብሰባ ሰፋ ያለ ውይይት አድርገዋል፤ ሕብረታቸውን ፈጥረዋል፤ ዳግም ላይሸነፉ፣ ጠላትን ከሀገራቸው ሳያስወጡ ወደኋላም ላይመሰሱም ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡

የጦር ግንባራቸውን ተከፋፍለው ሥምሪት ከመውሰዳቸው አስቀድሞ ግን ሀገሪቱን ነፃ ያደረገ፤ ዓለም አቀፍ እውቅናም ያጎናጸፈ የኢትዮጵያ አርበኞች ብሔራዊ ማኅበርን ለመጀመሪያ ጊዜ በዚች ቦታ መሰረቱ፡፡ ጦርነቱን አቀጣጥለውም ፋሽስት ጣልያንንም ዳግም ላይመለስ አሳፍረው ወደመጣበት መለሱት፡፡ አንዲት ግራር ላይ በተነደፈ የጦር ስትራቴጂ ኢትዮጵያውያን አባቶች ነፃነታችንን አወጁ፡፡

አንዲት ግራር በርካታ ክዋኔዎች ይከወኑባት ነበር፡፡ ለረጅም ዘመናት በደም ሲፈላለጉ የነበሩ ሰዎች እርቀሰላም አውርደውበታል፡፡ ለአካባቢው ማኅበረሰብም መሰብሰቢያ ማዕከል ነበረ፡፡

በጥቅሉ አንዲት ግራር የሀገር ፍቅር ስሜት የተንጸባረቀበት ታሪካዊ ቦታ ነው፡፡ ዛፏ የእድሜ ጣርያዋ ደርሶ በ2006 ዓ.ም ክረምት ላይ ወድቃለች፡፡ ነገር ግን የተስተናገደባትን ታሪካዊ ክስተት ለትውልድ ማስተማር እንዲቻል ለቱሪዝም መዳረሻነት ተከልሏል፡፡

በየዓመቱ ጥር 1 በዚች ታሪካዊ ቦታ የአርበኞች ክብር በደመቀ ሁኔታ ይዘከራል፡፡ በዚህ ቦታ የዛሬው ትውልድ ራሱን የሚያድንበት ታሪካዊ ትውፊት አለ፡፡ ከችግሮች ሁሉ መውጫ መሰላሉ እንደነ ራስ አበበ አረጋይ፣ ባላምባራስ ባሻህ ኃይሌ፣ ደጃዝማች ተሰማ እርገጤ፣ ፊታውራሪ ታደሰ በላይነህ እና ሌሎችም ተሰባስቦ መምከር ነው፡፡ ይህ ጥበብ አንዲት ግራር ላይ ይገኛል፡፡ አንዲት ግራር ዛሬም ለእኛ ታስፈልገናለች፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/