“አነጣጥረው የማይስቱ ዓይኖች፣ የማይታክቱ እጆች”

526

ታኅሣሥ 16/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጥያቄው ስንትና የት ላይ ልምታ? ነው። እንጂማ እስተዋለሁ ብሎ ስጋት የለም። ከፈለገው ቦታ ከፈለገበት ላይ ይመታል። ስንቶችን እንደመታ ቁጥሩን ማን ያውቃል? ብቻ ግን ዓልሞ እየተኮሰ እንዳልነበር ያደርጋቸዋል ይሉታል ጓደኞቹ። ተኩሶ መሳት አይታሰብም። መተኮስ መደምሰስ ነው መርሁ። አልሞ መምታት ብቻ ሳይሆን በፍቅር መኖርም ይችልበታል። ያገኘው ሁሉ አቅፎ ሳይስም አይለቀውም። ስሙን ጠርተው አይጠግቡትም። እርሱ መሳሪያውን ይዞ ብቅ ካለ ነገር አበቃ፣ በዚያ ግንባር ያለው ጠላት ወዮለት እየተነጠለ ይወድቃል፣ እየተመታ ያልቃል። ለጠላት ረፍት አይሰጥም፣ ምሽጉን ደርምሶ ጠላቱን አፈር አልብሶ ካልሆነ በስተቀር አያርፍም።
አጠብቆ ለሚወዳት እናት ሀገሩ፣ ክብርና ማዕረጉ ለሆነችው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሠንደቁ ጠላትን ይጥላል። ሰንደቋን ደፍሮ፣ ክብሯን ነክቶ መኖር የሚቻለው የለምና እርሱም የደፈሯትን፣ የነኳትን፣ ጦር ያዘመቱባትን እየነጠለ ይጥላቸዋል።
ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ከዘመን ጋር የሚወዳጅ፣ ዘመኑን የሚዋጅ ጀግና ማብቀልን ታውቅበታለች፣ ቀደም ባለው ጊዜ ታንክና ፣ መድፍ በሌለበት፣ አየር በሰማይ ባላንዣበበት በዚያ ዘመን በፈረስ እየተምዘገዘጉ፣ በቃታ ብረት የሚነጥሉ፣ በሳንጃና በጎራዴ የሚዘነጥሉ ጀግኖች ነበሯት። ዘመናዊ መሳሪያ ይዞ የሚነሳውን ጠላት ፈረስ እያሰገሩ፣ በጋሻ እየመከቱ በጦር ይወጉት፣ ልኩን ያሳዩት፣ ክንዳቸውን ያቀምሱት ነበር። ከጎራዴያቸው እና ከሳንጃቸው አምልጦ የሚተርፍ አልነበረም። ዘመንን የሚዋጁ ጀግኖች መውለድ ታውቅበታለችና እርሷን አሸንፎ በምድሯ የኖረ አልተገኘም። አይገኝምም።
እርሷ ጀግና እንደ ቡቃያ የሚበቅልባት፣ ደፋር እንደ ችግኝ ተኮትኩቶ የሚያድግባት፣ ልበ ሙሉ በኩራት የሚኖርባት፣ እልፍ መራር ልብ ያላቸው ጀግኖች ያሉባት ናት። ዘመኑን የሚዋጁ ጀግኖች ተፈጥረዋል። ከአባቶቻቸው በተቀበሉት ጀግንነት፣ በወረሱት አሸናፊነት ባካበቱት ልበ ሙሉነት ጠላትን ድባቅ ይመታሉ፣ ሀገርን ነፃ ያወጣሉ። ድልን ከፍ አድርገው ይሰቅላሉ። ጠላትን ዝቅ አድርገው መቀመቅ ውስጥ ይጥላሉ። የቀደሙት አባቶች ጀግንነት ወራሽ፣ ከዛሬ መራዥ ተኳሽ ጋር ተገናኝተናል።

የጀግኖች የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባል ነው። በሠራዊቱ ውስጥ ጀግንነት ውርስ፣ ድል ማድረግ ልብስ ነውና ሁሉንም በጀግንነት ያደርጋሉ። ሁሉንም በድል ይወጣሉ። ማሸነፍ ነው መልሳቸው፣ ድል ማድረግ ነው መገለጫቸው። የእነዚህ ጀግኖች አባል ነው እኛ ያገኘው ጀግና። የአየር መቃወሚያ (ዙ 23) ተኳሽ ነው። ተኳሹ በሰማይ ላይ እንኳን አየር ወፍ እንዳትበር ያደርጋል ይሉታል ጓደኞቹ። የሚተኩሰውን መሳሪያ ለምድር መዋጊያ ተጠቅሞበታል። ጠላት መትቶበታል፣ ምሽግ ሰብሮበታል፣ ጠላት ጥሎበታል። ሀገር ነፃ አድርጎበታል። ኢትዮጵያ አየር የሚጠቀም የውጭ ጠላት ቢገጥማት ከዚህ ጀግና እይታ አያመልጥም ነው የሚሉት። በታየ በሰከንዶች ውስጥ ከምድር ጋር ይደባልቀዋል ይሉታል ጓደኞቹ። እንዴት ካሉ ዒላማ ተሰጥቶት አይስትምና ነው። አነጣጥረው የማይስቱ ዓይኖች ፣ የማይታክቱ እጆች አሉት። የአየር መቃወሚያውን በየትኛውም አቅጣጫ እያሽከረከረ ጠላት ያለበትን ቦታ ይደበድባል። ባዶ ያደርጋል። የጠላትን ምሽግ በሬሳ ይሞለዋል።
ምክትል አሥር አለቃ ስንዴው ዳምጠው ይባላል። መሠረታዊ ውትድርናን በብርሸለቆ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ወስዷል። የአየር መቃወሚያ ስልጠናውን ደግሞ በአዋሽ አርባ ወስዷል። በማሰልጠኛ ቆይታው ብዙ መልካም ነገሮችን ተምሯል። “በማሰልጠኛ ተቋም ስለ ሀገር ፍቅር ተምሬአለሁ። ሀገሬን እንድወድ አድርገው ነው ያሰለጠኑኝ። ለዚያም ሀገሬን እያገለገልኩ ነው። በማሰልጠኛ ተቋም ምርጥ እውቀት ጨብጠናል። እውቀታችንንም ሜዳ ላይ አላበከንም፣ ተጠቅመንበታል። ዙ 23ን ለምድር ዒላማም እንጠቀምበታለን። ጥሩ አጉራሽ፣ ጥሩ ተኳሽ፣ ጥሩ ሹፌር ካለ ዙ 23 አይስትም። ጠላትን ይደመስሳል። እኛም ጠላትን ደምስሰንበታል። ሀገርም ነፃ አድርገንበታል” ነው ያለው ምክትል አሥር አለቃ ሠንዴው።

በተሰለፈባቸው አውደ ውጊያዎች ሁሉ ጠላትን ድባቅ መትተዋል። ጠላትን እንዳልነበር አድርገዋል። የጠላትን ከባድ መሳሪያዎች ወደ አመድነት ቀይረዋል። ማን ይያዘኝ፣ የሚያቆመኝ ምድራዊ ኀይል የለም ሲል የነበረው ጠላት ዛሬ ላይ በጀግኖቹ ተመትቶ የት በገባሁ፣ የት በደረስኩ ድረሱልኝ እያለ ነው። “አንዳንድ ሰው መከላከያ ሲባል ሁልጊዜ ውጊያ፣ ሁልጊዜ ሞት ያለ ነው የሚመስለው። ጓደኞቼ ከቤተሰቦቼ በላይ ናቸው፣ ብቆስል ያክሙኛል፣ ብታመም ያስታምሙኛል፣ የትም ሁን እንደ መከላከያ ፍቅር የለም። መከላከያ ለእኔ ሕይወቴ ነው። ሀገርህንም እናትህንም የምታገኘው መከላከያ ውስጥ ነው። ዘለዓለም መከላከያ ሆኜ ብቆይ ደስ ይለኛል።” ምክትል አሥር አለቃ ስንዴው የመከላከያ ሕይወት በጣም ተወዳጅ፣ ሁሉ ነገር መሆኑንም ይገልፃል።
ወጣቶች ሁሉ መከላከያ ፍቅር እንደሆነ ተረድተው ተወዳጁን ተቋም እንዲቀላቀሉም መክሯል። አንድ ሰው አድነህ መሞት ጀግንነት መሆኑንም ይናገራል። መከላከያ ከራስ በላይ ለሕዝብና ለሀገር ይኖራል፣ ጠላት ግን ለራሱ የሚኖር ነው ይለዋል። መከላከያ መግባት ብረት ተሸክሞ መንቀሳቀስ ብቻ አይደለም። ብዙ እውቀቶች ያሉበት ተቋም ነው ይላል። ወጣቶች ሀገራችሁን አገልግሉም ነው ያለው ምክትል አስር አለቃ ስንዴው። አባቶቻችን በጦር በጎራዴ ያቆዩልንን ሀገር ወጣቶች ተቀብለው ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ አለባቸው ነው የሚለው።

በገቡባቸው አውደ ውጊያዎች ጠላት አስከሬን እየቆጠረ ይሸሽ እንደበር ያስታውሳል። ምክትል አሥር አለቃ ስንዴው ጠላትን ረግጦ የመግባት ድፍረትና ወኔ ያለው መሆኑንም ጓደኞቹ ይመሰክሩለታል። እርሱም እኔ የምዋጋው ለሀገሬ እንጂ ስሜ እንዲነሳልኝ አይደለም ይላል። ለሀገሬና ለሕዝቤ ብሰዋ ደስ ይለኛል ክብሬ ነው ይላል። “ኢትዮጵያ ማለት ለእኛ ደማችን ናት፣ ኢትዮጵያ እናቴ ናት። “ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚመጣ ኀይል አንታገሰውም። በምክር ከሰማ እንመክረዋለን። እምቢ ካለ ግን መውሰድ የሚገባንን እርምጃ እንወስዳለን። ሀገራችንንም ሰላም እናደርጋለን። ኢትዮጵያ እኛ እያለን መቼም አትፈርስም ” ነው ያለው።
የምክትል አስር አለቃ ረዳት ተኳሽ የነበረ እና አሁን ላይ ዋና ተኳሽ የሆነው ምክትል አስር አለቃ ታሪኩ ተስፋዬ ሀገር መጠበቅ ክብር ነው፣ ኢትዮጵያ ምስጢሯ ብዙ ነው፣ ጀግኖች አባቶቻችን በጎራዴ ነው የጠበቁልን፣ ለኢትዮጵያ ስል ፈንጅ ረግጣለሁ ከሁሉም በፊት ሀገር ትቀድማለች ብሏል። ምክትል አስር አለቃ ስንዴው በጉና ውጊያ ስናይፐር አንስቶ በመዋጋት ጠላትን እንዳበራየም መስክሮለታል።
መከላከያ ሰራዊት ፍቅር ነው፣ ሰው በእንቅፋት ይሞታል፣ ለሀገር መሞት ግን ክብር ነው ብሏል።
የዙ 23 አዛዥ ሀምሳ አለቃ ታደሰ ቶሌራ አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን አማርሮት ከመከላከያ ወጥቶ እንደነበር ያስታውሳል። እነርሱ በመከላከያ ላይ ጥቃት ሲፈፅሙ በድጋሜ መከላከያ ሰራዊትን መቀላቀሉን ነው የተናገረው። የዙ 23 ተኳሽ ልጆቼ ጀግኖች ናቸው። ከእነርሱ ጋር በመሥራቴ ኩራት ይሰማኛል። ጠላትን ባገኘንበት ቦታ ሁሉ ጨፍጭፈነዋል ነው ያለው። ጠላት ቁስለኛውን ማንሳት አልቻለም። የትግራይ እናቶች አስከሬኑን ቢያዩ ምን ሊሉ እንደሚችሉ ሳስበው ይገርመኛል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሀገርና ሕዝብ የሚጠብቅ ኩራት መሆኑንም ገልጿል። ኢትዮጵያን በጉልበት አፈራርሳለሁ ለሚል አካል አንተኛም፣ ጠላትንም እረፍት እንነሳለን ነው ያለው። ሀምሳ አለቃ ታደሰ በነበረው አውደ ውጊያ የደብረታቦር ከተማ ሕዝብ ወታደር ነበር ብሏል። ጀግና ሕዝብ ነው፣ አንድም ቀን የወንዝ ውኃ ጠጥተን እና ኮቸሮ በልተን አናውቅም ምሽግ ድረስ እየመጡ ስንቅ ያቀብሉናል። ምስጋና ያንስባቸዋል። ለዚህ ሕዝብ የማንከፍለው መስዋእትነት የለም። ጠላትን ጉድጓድ ውስጥ ገብተን እናወጠዋለን ነው ያለው። የኢትዮጵያ ጀግኖች ለእናት ሀገራቸው ሁሉንም ነገር እየሰጡ ነው። ለእናት ሀገራቸው በምሽግ ያድራሉ፣ ለእናት ሀገራቸው ረሀብና ጥሙን ይችላሉ። ችግሩን ተቋቁመው በድል ይራመዳሉ። አሁንም እየተራመዱ ነው።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation