ደብረ ታቦር፡ ግንቦት 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በካናዳ ሀገር የሚኖሩ አቶ ማርቆስ ዘውዱ የሚባሉ በጎ አድራጊ በለገሱት 10 ሚሊዮን ብር ለደብረታቦር ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተገነባ የድንገተኛ ህክምና መሥጫ ሕንጻ ተመርቋል።
በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ እና በደብረታቦር ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የድንገተኛና ጽኑ ህሙማን ስፔሻሊስት ዶክተር ሞላልኝ ውባንተ ህንጻው በመገንባቱና የህክምና ቁሳቁስም በመገኘቱ የነበረውን የህሙማን ማቆያና ማከሚያ ችግር እንደሚቀርፍ ተናግረዋል።
የሆስፒታሉ የቦርድ ሰብሳቢና የደብረታቦር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ደሳለኝ በላቸው ባደረጉት ንግግር በጎ አድራጊ ግለሰቡ ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል። ሌሎችም ተመሣሣይ ድጋፍ እንዲያደርጉ አሣሥበዋል።
ለህክምና ክፍሉ መገንባት ድጋፉን የለገሱት አቶ ማርቆስ ዘዉዱ የአባታቸውን የአቶ ዘውዱ ተገኘን በጎ ምግባር ለማስቀጠልና ለማሥታወስ ያደረጉት ድጋፍ እንዲሳካ ያበረታቷቸውን ወዳጅ ዘመዶቻቸው አመሥግነዋል።
አቶ ማርቆስ ለመገንቢያ የተሰጣቸውን ቦታ በ6 ወር ውስጥ በ 10 ሚሊዮን ብር ወጪ ገንብተውና የውስጥ ቁሳቁስ አሟልተው መጨረሳቸውን ገልጸዋል። በውጪ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም እንደየአቅማቸው ወገናቸውን እንዲያግዙ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል አቀፍ ልማት ማኀበር (አልማ) ሥራ አስኪያጅ አቶ መላኩ ፈንታ በመልእክታቸው አቶ ማርቆስና አባታቸው ያደረጉት የልማት ድጋፍ ባለውለታ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!