አሸባሪው ትህነግ የጀመረውን ጦርነት ለመመከት ሁሉም ኅብረተሰብ ከጸጥታ አካላት ጎን እንዲሰለፍ መንግስት ጥሪ አቀረበ።

0
350

አሸባሪው ትህነግ የጀመረውን ጦርነት ለመመከት ሁሉም ኅብረተሰብ ከጸጥታ አካላት ጎን እንዲሰለፍ መንግስት ጥሪ አቀረበ።

አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 08/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ በሰሜን ጎንደር፣ በደቡብ ጎንደር፣ በሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ወሎ፣ በዋግኽምራና በአፋር አሰቃቂ ግፍ ፈጽሟል። የሃይማኖት አባቶችንና ንጹሃንን ግድሏል። የአርሶ አደሩን የኢኮኖሚ አቅም ለማዳከም አዝመራ ጭፍጭፏል። አንስሳቱን ገድሏል። ከአማራ ጋር ሂሳብ አወራርዳለሁ እንዳለው በቻለው ሁሉ የዘር ማጥፋትን ፈጽሟል።

አሸባሪው ትህነግ ከሰሞኑም በውጫሌና ጭፍራ አካባቢዎች ላይ በፈጸመው የከባድ መሳሪያ ጥቃት ከ30 በላይ ንጹሃን መግደሉን የመንግስት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ አሸባሪው ትህነግ ከሰሞኑ በውጫሌና ጭፍራ አካባቢዎች በከባድ መሳሪያ በፈጸመው ጥቃት ንጹሃንን ገድሏል። በርካታ ዜጎችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል።

የሽብር ቡድኑ የጀመረውን ጦርነት ለመመከት ሕብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጎን በመሆን ከአካባቢው ሳይለቅ መመከት እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል።

አሻባሪው ትህነግ በተከታታይ በሚፈጽማቸው ጥቃቶች ህዝብን ለከፋ አደጋ እየዳረገ ከመሆኑም በላይ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የእርዳታ እህል እንዳይደርስ እያደረገ መሆኑም ይታወቃል።

መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ተግባራዊ ካደረገ በኋላ አሸባሪው ህወሃት በአጎራባች ክልሎች የተለያዩ ጥቃቶች በመፈጸም በዜጎች ላይ ከፍተኛ አካላዊና ቁሳዊ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።

ሚኒስትሩ በመግለጫቸው፤ አሸባሪው ህወሃት በደቡብ ወሎ፣ በአምባሰልና ውጫሌ እንዲሁም በአፋር ጭፍራ ዳግም ጥቃት መክፈቱን ተናግረዋል።

ጥቃቱ በከባድ መሳሪያ የታገዘ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በዚህም 30 ንጹሃን ሲገደሉ በርካታ ሰዎች ደግሞ መፈናቀላቸውን አብራርተዋል።

አሸባሪው ህወሃት ህጻናትን፣ ሴቶችን አዛውንቶችንና የጦር ጉዳተኞችን ከፊት በማሰለፍ ከኋላ ደግሞ ከባድ መሳሪያ የታጠቁትን በማስከተል ጥቃት እያደረሰ እንደሆነም ነው የጠቆሙት።

አሸባሪው የከፈተው ጦርነት ህዝባዊ መሆኑንም አመልክተዋል።

በመሆኑም በየአካባቢው ያሉ ወጣቶችና ሕብረተሰብ አካባቢውን ሳይለቅ በንቃት በመጠበቅ “አሸባሪውን እንዲመክት መንግሥት ጥሪ ያቀርባል” ሲሉም አመልክተዋል።

ዘጋቢ:–አንዷለም መናን

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m