አሸባሪው ትህነግ በደብረታቦር ሕዝብ ላይ የፈጸመው የከባድ መሳሪያ ድብደባ የአማራ ሕዝብን በጠላትነት መፈረጁን በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

0
229

ባሕር ዳር: ነሐሴ14/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ ከምስረታው ጀምሮ አማራን በጠላትነት ፈርጆ በመንቀሳቀስ በማንነቱ ብቻ ለይቶ ጨፍጭፏል፣ አፈናቅሏል ብሎም የተለያዩ ግፎችን ፈጽሟል፤ እየፈጸመም ይገኛል።

አሸባሪ ቡድኑ ከአማራ አልፎም የኢትዮጵያውያን ጠላት መሆኑን አሳይቷል። ዛሬም እኩይ ተግባሩን ቀጥሎበታል።

ትናንት አሸባሪው ትህነግ በደብረ ታቦር ከተማ ባስወነጨፈው ከባድ መሳሪያ በአንድ ቤት ውስጥ በነበሩ 5 የቤተሰብ አባላት የሞት፤ በ2 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት እንዳደረሰና ግምቱ ያልታወቀ የግለሰቦች ንብረትም መውደሙን መዘገባችን ይታወሳል። አሁን ላይ በወጡ መረጃዎች ደግሞ ጥቃቱ በደረሰባቸው ቤተሰቦች ቤት ተከራይቶ ይኖር የነበረና ከባድ ጉዳት የደረሰበት አንድ ግለሰብ ህይወቱ አልፏል።

አሚኮ አሸባሪው ትህነግ በፈጸመው ጥቃት በሕይወት የተረፉ የቤተሰብ አባልና ነዋሪዎችን በቦታው ተገኝቶ አነጋግሯል።

አቶ ድረስ ነጋ በጥቃቱ አምስት ቤተሰባቸውን አጥተዋል። ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት ቤተክርስቲያን የነበሩት አቶ ድረስ ልጆቻቸውን፣ ባለቤታቸውንና ተከራያቸውን እንዳጡ ተናግረዋል። በዚህም ሽብርተኛ ቡድኑ በፈጸመው ጥቃት መሪር ሐዘን እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።

አሸባሪው ትህነግ በደብረታቦር ሕዝብ ላይ የፈጸመው የከባድ መሳሪያ ድብደባ የአማራ ሕዝብን በጠላትነት መፈረጁን በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

አቶ ምህረት ነጋ የተጎጂ አባወራ ታናሽ ወንድም ናቸው። የአካባቢው ማኅበረሰብ ከማጽናናት ባለፈ የፈራረሱትን ቤቶች እየጠገነ መሆኑን ተናግረዋል።

የከተማዋ ነዋሪ አቶ ዋጋዬ ይመር የአካባቢውን ኅብረተሰብ በማስተባበር የፈራረሱ ቤቶችን እያስጠገኑ ነው ያገኘናቸው።

አቶ ዋጋየ እንዳሉት ሽብርተኛው የትህነግ ቡድን በሕዝቡ ላይ የፈጸመው የከባድ መሳሪያ ድብደባ ንጹሐንን ቢገድልም ያሰበው ዓላማ እንደማይሳካለት ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ-: ቡሩክ ተሾመ – ከደብረ ታቦር

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m