አሸባሪው ትህነግ በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ላይ የሠራው ግፍ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይፋ እንደሚሆን ዶክተር አስራት አጸደወይን ገለጹ፡፡

0
100

አሸባሪው ትህነግ በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ላይ የሠራው ግፍ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይፋ እንደሚሆን ዶክተር አስራት አጸደወይን ገለጹ፡፡

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 24/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ዛሬ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች እያስመረቀ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ለተመራቂ ተማሪዎች እና ለክብር እንግዶች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ዶክተር አስራት ተመራቂዎች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተቋቁመው ለዚህ መድረሳቸው በቀጣይም በፈታኝ ሁኔታዎች ማለፍ እንደሚችሉ ማረጋገጫ ነው ብለዋል፡፡

ወቅቱ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት የተጠናቀቀበት መሆኑም ታላቅ ድል እንደሆነ አንስተዋል፡፡ ይህም በአድዋ የታየው ድል በህዳሴው ግድቡ መረጋገጡ የሀገሪቱ ታላቅነት ማሳያ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

የውስጥ እና የውጭ ጠላቶች ‹‹ይፈራርሳሉ›› ብለው ሲያሟርቱ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በስኬት መጠናቀቁ ለጠላቶች መርዶ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከጎረቤት ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች በተለይም ከኤርትራ፣ ከሶማሊያ፣ ከጅቡቲና ከደቡብ ሱዳን ጋር የእርስ በርስ ትስስር በመፍጠር ተማሪዎችን ተቀብሎ በውጭ ፕሮጀክት ድጋፍ በማስተማር ላይ እንደሆነም አንስተዋል፡፡

የወልቃይት ጠገዴ እና ጠለምት አማራ ሕዝብ ትክክለኛ ማንነቱ እና ወጉ ምን እንደነበር፣ ባለፉት አርባ ዓመታት የደረሰበትን የዘር ፍጅት፣ የኢኮኖሚ አሻጥር፣ በትምህርት እና በጤና ላይ የደረሰውን ግፍ በዝርዝር ጥናት ማካሄዱንም ዩኒቨርሲቲው ከሠራቸው ተግባራት ውስጥ ተጠቅሰዋል፡፡ የሥራ ውጤቱም በቅርቡ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይፋ እንደሚሆን አንስተዋል፡፡ ይህም በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ተደራሽ እንደሚሆን ዶክተር አስራት ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዓመት ዩኒቨርሲቲው በትብብር ከሚሠራባቸው ሰባት የሱዳን ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ ከሆነው የሱዳን ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመሥራት ተወካዮቻቸው መገኘታቸው እና ለተወዳጁ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን የክብር ዶክትሬት መሰጠቱ የዚህ ዓመት ምረቃ ካለፉት ዓመታት የተለየ እንደሚያደርገው አብራርተዋል፡፡

ከሱዳን ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሚደረገው ትብብር የሁለቱን ሀገሮች የቆየ የጋራ ትስስር እንደሚያጠናክርም አንስተዋል፡፡ በርካታ ሥራዎችንም በጋራ እየሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰዋል፡፡

ተመራቂ ተማሪዎችም በተማሩበት የትምህርት ዘርፍ ማኅበረሰቡን በቅንነት እንዲያገለግሉ እና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አምባሳደር ሆነው እንዲሰሩ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በዳግማዊ ተሰራ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m