አሸባሪው ትህነግ በሰሜን ጎንደር ዞን አዳርቃይ ወረዳ ዛሪማ ከተማ የሚገኘውን መስጂድ ማውደሙን የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ገለጸ፡፡

0
157
ጥቅምት 10/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪውና ወራሪው ትህነግ በወረራ በያዛቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች በንጹሐን ላይ ከፍተኛ ጭፍጨፋ ፈጽሟል፤ በርካታ ዜጎችን አፈናቅሏል፤ ሃብትና ንብረት ዘርፏል፤ መዝረፍ ያልቻለውን ደግሞ አውድሟል፤ ይህንኑ እኩይ ድርጊቱን አሁንም ቀጥሎበታል፡፡
የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን በኢትዮጵያውያን ዘንድ ትልቅ ክብር እና ቦታ የሚሰጣቸው የሃይማኖት ተቋማት ላይ ጭምር ውድመት እያደረሰ ይገኛል፡፡
አሸባሪውና ወራሪው ትህነግ ቡድን በሰሜን ጎንደር ዞን አዳርቃይ ወረዳ ዛሪማ ከተማ የሚገኘውን ትልቁ መስጅድ በከባድ መሳሪያ እንዳወደመው የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሐጂ ሙሐመድ ሐሰን ገልጸዋል። መስጂዱ ታሪካዊ እና በቅርቡ በሕዝብ ሃብት እድሳት የተደረገለት ነው ያሉት ሐጂ ሙሐመድ ስለውድመቱ ደግሞ ከሁለት ቀናት በፊት ለምክር ቤቱ መረጃ መድረሱንም አስታውቀዋል።
ዋና ጸሐፊው እንደገለጹት አሸባሪው ትህነግ በአምልኮ ቦታዎች ላይ እያደረሰ ያለው ውድመት ሀገር ከማፍረስ ጎን ለጎን ኅብረተሰቡን ያለ ሃይማኖት ተቋማት እንዲቀር በማሰብ ነው፤ የዛሪማ መስጂድ ውድመትም ለዚህ ማሳያ ነው። ሽብርተኛው ትህነግ በርካታ መስጂዶችን እንዳወደመ በርካታ መረጃዎች እየወጡ ነው ያሉት ሐጂ ሙሐመድ በቀጣይም ጉዳት የደረሰባቸው ተለይቶ ትውልዱ የሽብር ቡድኑን የጥፋት ልክ በውል እንዲገነዘብ ይደረጋልም ብለዋል፡፡
ሽብርተኛው ትህነግ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ትምህርት ሲከታተሉ የነበሩ ተማሪዎችንም ጨፍጭፏል ነው ያሉት ዋና ጸሐፊው፡፡
ዋና ጸሐፊው እንደተናገሩት ሽብርተኛው ትህነግ በሃይማኖት ተቋማት ላይ የሚያደርሰው ጥቃት ለሃይማኖት ከፍተኛ ጥላቻ ያለው መሆኑን ማሳያ ነው፡፡ የሃይማኖት ተቋማትን የጦር ካምፖች አድርጓል፤ ይህም አስነዋሪና አስጸያፊ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
ኹሉም ሰው ወንጀሉን በወሬ ሳይሆን በተግባር እያየ በመሆኑ አባቶች በፀሎት፣ ወጣቶች በጉልበት፤ ሃብት ያላቸው ደግሞ በገንዘባቸው በማገዝ ሽብርተኛው ትህነግ የሚያደርሰውን ጥቃት መከላከል ይገባል ብለዋል፡፡
ሐጂ ሙሐመድ ሕዝበ ሙስሊሙ ከፀጥታ ኀይሉ ጎን በመሰለፍ ሽብርተኛው እና ወራሪው ትህነግን ሊፋለመው ይገባል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ