አሸባሪው ትህነግ በሰሜን ወሎ አካባቢዎች እያደረሰ ያለው ግፍ በተፈናቀሉ የዓይን እማኞች አንደበት…

0
65
መስከረም 28/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጥላቻ ያናወዘው እና እብሪት ያደነዘዘው የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን ኢትዮጵያን ከጀርባዋ ከወጋት ውሎ አድሯል፡፡ ሽብርተኛው ትህነግ በወረራቸው አካባቢዎች ሁሉ ግፍ እና በደል እየፈጸመ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ነውሩን በግልጽ እያሳየም ነው፡፡ ምንም እንኳን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሽብርተኛው ትህነግን እኩይ ተግባራት እያየ እንዳላየ ቢያልፈውም በየቀኑ የሚፈጽማቸውን ድርጊቶች በማውገዝ ከኢትዮጵያ ጎን ለመቆም ከበቂ በላይ ምክንያቶች ነበሩ፡፡
ሽብርተኛው ትህነግ በአማራ ክልል በከፈተው ወረራ እየደረሰ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ አስደንጋጭ የሚባል ነው፡፡ አረጋዊያን እና አቅመ ደካሞች የጦርነት ሰለባ ሆነዋል፡፡ ሕጻናት እና እናቶች በግፍ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ወጣቶች እና ታዳጊዎች በበርካታ አካባቢዎች በተናጠል እና በቡድን በግፍ ተጨፍጭፈዋል፡፡ ከዘረፋ የተረፉ እንስሳት ሳይቀሩ እየተገደሉ ነው፡፡ ነፍሰ ጡር እናቶች ከሰብዓዊነት በታች በወረደ መንገድ በጫካ እና በየመንገዱ ለመወልድ ተገድደዋል፡፡ሴቶች አስገድዶ መደፈር ተፈጽሞባቸዋል፡፡
ትምህርት ቤቶች፣ የጤና እና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ክፉኛ ወድመዋል፡፡ የግለሰቦችና የመንግሥት ሃብትና ንብረት ተዘርፏል፤ ወድሟል፡፡
ከኢትዮጵያውያን ነባር መንፈሳዊ የሥነ ልቦና ሥሪት በተፃራሪ የሃይማኖት ተቋማት የጦርነት አውድማ ሆነዋል፣ ተዘርፈዋል እንዲሁም ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
ከዓለም አቀፍ የጦርነት መርህ ባፈነገጠ መልኩ የመሰረተ ልማት አውታሮች ተጎድተዋል፡፡
አሸባሪው እና ወራሪው የትህነግ ቡድን አሁንም ድረስ በወረራቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች የዜጎችን ሰላማዊ እንቅስቃሴ የሚያውኩ፣ እምነትን የሚዳፈሩ፣ ባህላዊ፣ መንፈሳዊ እና ታሪካዊ ቅርሶችን የሚጎዱ ሕገ-ወጥ ተግባራትን እየፈጸመ ነው፡፡
የሽብር ቡድኑ እየፈጸመው ያለው ድርጊት አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል የሚሉት ከቆቦና አካባቢው የተፈናቃሉ የዓይን እማኞች በተወረሩ አካባቢዎች የሚኖረው ሕዝብ በቀላሉ ከጉዳቱ እንዳያገግም በማሰብ የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ያለውን ሰብል ዘረፋ ለመፈጸም እየተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡ ወቅቱ በቆቦ አካባቢ ቡንኝ፣ ማሾ እና ሌሎች ሰብሎች የሚደርሱበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የአርሶ አደሩን ሰብል ለመዝረፍ ማጭድና የሰው ኃይል በቆቦ እና ላልይበላ አካባቢ በተሸከርካሪ ጭነው አምጥተው ሲያራግፉ አይተናል ነው ያሉት፡፡ እስካሁን የደረሰው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት አላንስ ብሎ ተጨማሪ ጥፋት ለመፈጸም በዝግጅት ላይ ናቸው የሚሉት የዓይን እማኞች የአርሶ አደሩን ሰብል በጊዜ መታደግ ካልተቻለ ለተጨማሪ ዓመታት ተረጂ እንሆናለን ነው ያሉት፡፡
አሸባሪው ቡድን እያደረሰ ያለው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ሲያሰጋቸው በእግራቸው የተለያዩ አካባቢዎችን እያቆራረጡ ልጆቻቸውን ይዘው ወደ መቄት የደረሱት በቅርቡ እንደሆነ የዓይን እማኞች ነግረውናል፡፡
በቆይታችን ዓይናችን እያየ ሃብት እና ንብረታችን ተዘርፏል የሚሉት የዓይን እማኞቹ በመጨረሻ ቤተሰባቸውን ርሃብ ከሚግድልባቸው እየተጓዙ መሞት ይሻላል ብለው እንደወጡ ነግረውናል፡፡
የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን አባላት በየግለሰቡ ቤት እየገቡ ብር፣ ጌጣጌጥ፣ የዕለት ምግብ፣ ቴሌቪዥን፣ ልብስ እና መሰል መጠቀሚያ ቁሳቁስ ዘርፈዋል ብለዋል፡፡
የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን አባላት ፍላጎታቸው በመግደልና በማፈናቀል የከተማ እና የአካባቢው ሕዝብ መኖሪያ ቀየውን ለቆ እንዲወጣ እና በምትኩ የእነርሱን ሰዎች እንዲሰፍሩበት ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
የዓይን እማኞች እንደሚሉት የቆቦ ጊራና መስኖ ልማት ፕሮጀክት በሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን አባላት ሙሉ በሙሉ ተዘርፏል፡፡
የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን አባላት በሕጻናት እና ታዳጊዎች ላይ ሳይቀር የበቀል በትር በየቀኑ እያሳረፈ መሆኑንም በምሬት ገልጸዋል፡፡ የሚናገሩት ጸያፍ ንግግር እና የሚፈጸሙት አስነዋሪ ድርጊቶችም የሽብር ቡድኑ ምን ያክል በጥላቻ እንደሰከረ አመላካች ናቸው ነው ያሉት ፡፡
የዓይን እማኞቹ በላል ይበላ፣ ወልድያ እና ቆቦ አካባቢ የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን አባላት ከትግራይ ክልል ነዋሪዎችን እያመጣ እያሰፈረ እና ሕዝብ እያፈናቀለ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
የተዘጉ የግለሰብ ቤቶች በሮቻቸው እየተሰበሩ አዳዲስ ሰዎች እንዲገቡባቸው እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከመቄት
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ