አሸባሪው ሕወሓት ትንኮሳውን ወደሌሎች ክልሎች በማስፋቱ የእርዳታ እህል ለማጓጓዝ መቸገሩን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ፡፡

0
145

አሸባሪው ሕወሓት ትንኮሳውን ወደሌሎች ክልሎች በማስፋቱ የእርዳታ እህል ለማጓጓዝ መቸገሩን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ፡፡

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ሕወሓት መንግሥት ለሰብዓዊ ድጋፍ ሲል ያሳለፈውን የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔን ወደ ጎን በመተው ትንኮሳውን ወደ አማራ እና አፋር ክልል በማስፋቱ የእርዳታ እህልና ሌሎች ድጋፎችን ወደ ትግራይ ክልል ለማስገባት መቸገሩን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።

የተባበሩት መንግሥታት ቃል ዐቀባይ ፋርሃን ሀቅ እንደገለጹት፤ መንገድ በመዘጋቱ ምክንያት በተሽከርካሪዎች ሲጓጓዝ የነበረውን የእርዳታ እህል ወደ ትግራይ ክልል ማስገባት አልተቻለም።

ቃል ዐቀባዩ እንደተናገሩት፤ የእርዳታ ሠራተኞችን፣ ምግብ፣ ነዳጅ እና ሌሎች ሰብዓዊ አቅርቦቶችን የጫኑ ከባድ መኪናዎች ከሰመራ ከተማ ወደ ትግራይ በሚወስደው መንገድ ላይ ተዘግቶባቸው መንቀሳቀስ አለመቻላቸውንም ነው ቃል ዐቀባዩ የገለጹት።

ቃል ዐቀባዩ እንደገለጹትም በዚሁ ችግር ምክንያት እርዳታ ለሚፈልጉ የትግራይ ክልል ተረጂዎች መድረስ አልተቻለም።

በቀጣይ ቀናት የረድኤት ሰጪ ሠራተኞችን እና እንደ ነዳጅ ያሉ አቅርቦቶችን ወደ ትግራይ ማስገባት ካልተቻለ አንድ አንድ ሰብዓዊ ድጋፎች እንደሚቋረጡም ያለውን ስጋት ቃል አቀባዩ መግለጻቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

ድጋፉን በአውሮፕላን ለማድረግ በመንግሥት በኩል እድሉ እንደተመቻቸላቸውና እቅድ መያዙንም ጠቅሰዋል።

አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአፋር በኩል ወደ ትግራይ ክልል የእርዳታ እህል ጭነው የሚጓጓዙ ከባድ ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ የሽብር ጥቃት በመፈጸም የእርዳታ መስመር እንዲዘጋ ማድረጉን የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ባሳለፍነው ሳምንት ማስታወቁ ይታወሳል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ መቐለ 2ኛውን በረራ እንደሚያደርግ መንግሥት መግለጹም ይታወቃል።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here