“አሸባሪውን ቡድን ላይመለስ ሳንሸኝ እረፍትም፤ ምቾትም የለንም” አሸተ ደምለው

0
75

“አሸባሪውን ቡድን ላይመለስ ሳንሸኝ እረፍትም፤ ምቾትም የለንም” አሸተ ደምለው

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 29/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ወጣቶች ማኅበር ከዳንሻ ከተማ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡ ውይይቱም አሸባሪውን የትህነግ ቡድን ለመደምሰስ በሚደረገው የህልውና ዘመቻ እና በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

አሸባሪው የትህነግ ቡድን ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ ባደረሰው አስከፊ ጭቆና የዳንሻ ሕዝብ እና አካባቢው በርካታ መስዋእትነትን ከፍሏል ያሉት የአማራ ወጣቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት አባይነህ ጌጡ ዛሬ ላይ ለዘመናት የታገላችሁለት የማንነት ጥያቄ የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳይ ኾኗል ብለዋል፡፡

አሸባሪው ትህነግ ኢትዮጵያ ላይ የደቀነው የህልውና ስጋት መላው ኢትዮጵያዊያን የተገነዘቡት ሃቅ ነውም ብለዋል፡፡ አሸባሪው ትህነግ በስልጣን ላይ በቆየባቸው ዘመናት ካደረሰው ብዝበዛና ጭቆና ባሻገር በህልውና ዘመቻው በርካታ የዓለም ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ ፊታቸውን እንዲያዞሩ ያደረገውም በሀሰት ፕሮፖጋንዳ እንደኾነ አስገንዝበዋል፡፡

በመኾኑም ወጣቱ አካባቢውን ነቅቶ ከመጠበቅ እና የህልውና ዘመቻውን ከመደገፍ ባሻገር በማኅበራዊ ሚዲያው የሚደረገውን ዘመቻ በውል መገንዘብ እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡

የዳንሻ ከተማ እና አካባቢዋ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ከአሸባሪው ቡድን ስጋት ነፃ ለማድረግ ከጸጥታ ኀይሉ ጋር በመናበብ እየሠሩ መኾናቸውን የገለጹት ደግሞ የዳንሻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ስልጣን አድማሴ ናቸው፡፡ የአሸባሪው ቡድን አከርካሪ ከተመታበት ጊዜ ጀምሮ የኮንትሮባንድ ዝውውር መቀነስ የሚያመላክተው ቡድኑ ምን ያክል ለኢትዮጵያ ህልውና አደጋ እንደነበር ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ከንቲባው አሸባሪው ትህነግ ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ እስኪጸዳ ድረስ የኬላ ፍተሻን ማጠናከር እና ውስጥን ማጽዳት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሸተ ደምለው አሸባሪው የትህነግ ቡድን ተከዜን ሲሻገር መቃብር እንጅ ሀገር እንደማያገኝ ያውቀዋል ነው ያሉት፡፡ ሌላው የግፍ ዘመን ቢረሳ እንኳን ማይካድራ ላይ ለፈጸሙት ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተታቸው ማፈር በተገባቸው ነበር ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ነገር ግን አሸባሪው ቡድን ከስህተትም ኾነ ከሕይዎት መማር የማይችል በመኾኑ ልናስተምረው በቂ ዝግጅት አድርገናል ነው ያሉት፡፡ “እኛ ኢትዮጵያዊያን አሸባሪውን ቡድን ላይመለስ ሳንሸኝ እረፍትም፤ ምቾትም የለንም” ብለዋል፡፡

አቶ አሸተ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት የሕልውና ዘመቻ የሚመራበት የራሱ ሥርዓት እንዳለው በመግለጽ ግንባር ያለው ቡድን በትዕዛዝ ደጀን የኾነው ሕዝብ በስንቅና ትጥቅ የሚያደርጉትን መደጋገፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡ የአማራ ወጣቶች ማኅበር በዞኑ ባሉ ወረዳዎች በመዘዋወር ላደረጉት ድጋፍ እና አጋርነት ዋና አስተዳዳሪው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – ከዳንሻ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here