“አሸባሪውና ወራሪው ቡድን ይቀበራል፤ በዙሪያውም ያሉት ተልዕኮ ፈፃሚዎች እንደሚያፍሩ አትጠራጠሩ” ግንባር የሚመሩ የጦር መኮንኖች

0
160

መስከረም 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሚዲያዎች፣ ተቋማት ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች እንዲሁም ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን በደቡብ ጎንደርና በስሜን ወሎ ዞኖች ያወደመውንና የዘረፈውን ንብረት ተመልክተዋል።

የኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በመልክታቸው የኅብረተሰቡን የድጋፍ ንቅናቄ አድንቀናል ብለዋል። “ኅብረተሰቡ የቆሰሉትን እና የደከሙትን በመንከባከብ አይዟችሁ እያለ ሞራል በመስጠት ወገንተኝነቱን አሳይቷል፤ ዛሬም እንዳያችሁት የተዘጋጀ የዕለት ምግብን ጨምሮ ከኅብረተሰቡ አበረታች የሆነ ድጋፍ ለሰራዊቱ እየደረሰው ይገኛል” ብለዋል።

ሕዝቡ የደረሰውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት በዓይኑ በማየት የሽብር ቡድኑ ምን ያክል ጉዳት እንዳደረሰ ለመረዳት ችሏልም ብለዋል።

ኮሎኔል ጌትነት እንዳሉት የሚዲያና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ከዚህ ድረስ መጥተው ምልከታ ማድረጋቸው ለሠራዊቱ ከፍተኛ ሞራል ይሰጣል።

የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ምልከታም ሆነ የሕዝቡ ድጋፍ ለሰራዊቱ ትልቅ ስንቅ ነው ብለዋል። ይህን ክፉ ቡድን ለመደምሰስ የሚደረገው ድጋፍ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት የጦር መኮንኖች በበኩላቸው ጠላትን ለመደምሰስ በተለያየ መልኩ ሁላችንም ወደ ግንባር መሰለፍ አለብን ብለዋል።

“የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች እና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ግንባር ድረስ መጥታችሁ ስለተመለከታችሁን እናመሰግናለን ” ነው ያሉት

የጦር መኮንኖቹ አሸባሪውና ወራሪው ቡድን ይቀበራል፤ በዙሪያው ያሉ ተልዕኮ ፈፃሚዎችም እንደሚያፍሩ አትጠራጠሩ ብለዋል። ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር በመሆኗ በትናንሾች አታፍርም ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ-ከፍላቂት

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m