“አረጋውያን እናቶቻችን እና አባቶቻችን ከመሆናቸው ባሻገር የአንድ ሀገር ሀብት እና የዕውቀት ምንጭ፣ ታሪክ እና ጥበብ ስለሆኑ ልንከባከባቸው እና ልንደግፋቸው ይገባል፡፡” ዶክተር ሙሉነሽ አበበ

0
171

ባሕር ዳር፡ መስከረም 20/213ዓ.ም (አብመድ) ነገ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ30ኛ በሀገራችን ለ29ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአረጋውያን ቀን አስመልክቶ የአማራ ክልል ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ የአረጋውያን በዓል በሚከበርበት ወቅት ጧሪ እና ደጋፊ የሌላቸውን አረጋውያን ቋሚ በሆነ መልኩ የሚደገፉበት ሥርዓት መፍጠር እንደሚገባ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ አበበ (ዶክተር) አሳስበዋል፡፡

በአማራ ክልል 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን አረጋውያን እንዳሉ ኃላፊዋ ጠቁመዋል፡፡ 1 ሺህ 500 አረጋውያን በቋሚነት እየተደገፉ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡ “50 ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለ50 ሰው ደግሞ ጌጡ ነው” ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ አበበ እያንዳንዱ ሰው ለአረጋውያን ድጋፍ ቢያደርግ ችግሩ ሊፈታ እንዲሚችል አመላክተዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ለአረጋውያን የገቢ ምንጭ ማስገኛ በማሰብ በሁሉም ዞኖች የአረጋውያን መርጃ ማዕከላት እንዲገነቡ በመወሰኑ እስካሁን ዘጠኝ ዞኖች ቦታ ተረክበው እንቅስቃሴ መጀመራቸውን አብራርተዋል፡፡ የኮሮናቫይረስን ከመከላከል አንፃር በክልሉ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች የታቀፉ አረጋውያንን የመደገፍ ሥራ ሲሠራ መቆየቱንም ዶክተር ሙሉነሽ አበበ ጠቅሰዋል፤ ከችግሩ ስፋት እና ጥልቀት አንፃር ግን በቂ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

“አረጋውያንን የመንከባከብ ማኅበራዊ እሴቶቻችን እየተዳከመ ነው፤ ይህ ውብ የነበረው እሴታችን መልሶ እንዲንሰራሩ ማድረግ አለብን” ብለዋል ኃላፊዋ፡፡ በአማራ ክልል ጥቅምት 1/2013 ዓ.ም የአረጋውያን ቀን በምሥራቅ ጎጃም ዞን በሞጣ ከተማ አስተዳደር እንደሚከበር ጠቁመዋል፡፡ በወቅቱ በዞኑ የአረጋውያን ሕንጻ ግንባታን ለመደገፍ የታለመ መሆኑንም ኃላፊዋ ጠቅሰዋል፡፡

“ሁላችንም ከተባበርን የሚቸገሩ አረጋውያን፣ ወጣቶች እና ሕጻናት አይኖሩም“ ያሉት ኃላፊዋ “አረጋውያን እናቶቻችን እና አባቶቻችን ከመሆናቸው ባሻገር የአንድ ሀገር ሀብት እና የዕውቀት ምንጭ፣ ታሪክ እና ጥበብ በመሆናቸው ልንከባከባቸው እና ልንደግፋቸው ይገባል” ብለዋል፡፡

ጥቅምት 1/2013 ዓ.ም በምሥራቅ ጎጃም ዞን በሞጣ ከተማ አስተዳደር የሚከበረው የአረጋውያን ቀን እና ለሚገነባው የአረጋውያን መርጃ ማዕከል ሁሉም የክልሉ ማኅበረሰብ፣ የአካባቢው ተወላጆች እና ተቋማት ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሁሉም ዞኖች የሚገነቡት የአረጋውያን ሕንጻዎች አረጋውያን ወደ ልመና እንዳይወጡ ጉልህ አስተዋፅዖ እንደሚኖራቸው የአማራ ክልል አረጋውያን ማኅበር ፕሬዝዳንት ነፃነት ደስታ ተናግረዋል፡፡ አቶ ነፃነት “አረጋውያንን ወጣቶችን፣ ሕጻናትን፣ አካል ጉዳተኞችን አቅፎ ሲደግፍ የቆየው ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ነበር፤ ነገር ግን ይህ ተግባር የሁላችንም ኃላፊነት መሆን አለበት“ ብለዋል፡፡

እንደፕሬዝዳንቱ መግለጫ በሁሉም ዞኖች አሁን በመገንባት ላይ ያሉ እና ወደፊት ለመገንባት የታቀዱት የአረጋውያን የገቢ ማስገኛ ሕንጻዎች ተገንብተው ከተጠናቀቁ አረጋውያንን ለድህነት ከመጋለየጥ ይታደጋሉ፡፡

ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here