“አረንጓዴው የሀገር ዘብ ትኩረት ይሻል”

0
246

“አረንጓዴው የሀገር ዘብ ትኩረት ይሻል”
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 25/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል አካባቢ ደን እና ዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን መረጃ
እንደሚያመላክተው በአማራ ክልል አስራ ሦስት ፓርኮች እና የማኅበረሰብ ጥብቅ ደኖች ይገኛሉ፡፡ ከስሜን ተራራዎች ብሔራዊ
ፓርክ በስተቀር አስራ ኹለቱ ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት ሕጋዊ እውቅና ያገኙ ናቸው፡፡ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ እና
አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ በፌዴራል መንግሥት የሚተዳደሩ ሲሆን የተቀሩትን ክልሉ እያሥተዳደራቸው ይገኛል፡፡
በክልሉ ከሚተዳደሩት ፓርኮች ውስጥ የጎደቤ ፓርክ አንዱ ነው፡፡ ፓርኩ በምዕራብ ጎንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ጎደቤ
በተባለው ስፍራ ይገኛል፡፡ ጎደቤ ፓርክ ከባሕር ዳር 411 ኪሎ ሜትር፣ ከጎንደር ደግሞ 237 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከወረዳው ዋና
ከተማ አብርሃጅራ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ 18 ሺህ 987 ሄክታር መሬት ይሸፍናል፡፡ ፓርኩ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ
በክልሉ መንግሥት በጥብቅ ደንነት ተከልሎ ሲጠበቅ ቆይቷል፡፡ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በብሔራዊ ፓርክነት ተመዝግቧል፡፡
በኢትዮ-ሱዳን ድንበር አካባቢ የሰሃራ በርሃን መስፋፋት ከሚመክቱ አረንጓዴው ቀበቶ (ግሪን ቤልት) እየተባሉ ከሚጠሩ ፓርኮች
እና የደን አካባቢዎች ውስጥ አንዱ ነዉ። በውስጡ ከ27 በላይ እንደ የቆላ አጋዘን፣ ነብር፣ ተራ ቀበሮ፣ ድኩላ፣ ሚዳቋ፣ ጅብ፣
ዝንጅሮ፣ ቀይ ጦጣ፣ አነር እና መሰል ብርቅዬ የዱር እንስሳት ይገኙበታል፡፡ እንደ ነጭ ደርባን፣ የአፍሪካ ጥንብ አንሳ፣ (ሬድ ፉትድ
ሳልኮን) እና ከ 57 በላይ የተለያዩ የአዕዋፍ ዝርያዎች መኖሪያ ነው፡፡
የጎደቤ ፓርክ በአፍሪካ ደረጃ እየተመናመነ እንደመጣ የሚነገረው የእጣን ዛፍ፣ ለቅርፃ ቅርጽ አገልግሎት ከፍተኛ ጠቀሜታ
ያላቸውና በአፍሪካ ሀገራት በተለይም ደግሞ በኬኒያ እና ታንዛኒያ በብዛት እንደሚገኝ የሚነገረው የዞቢ እና የቆላ ቀርቀሃ ወይም
ሽመልን ጨምሮ ከ81 በላይ የዕፅዋት ዓይነቶች መገኛም ነው፡፡
የዚህ ሁሉ እምቅ ሀብት ባለቤት የሆነው የጎደቤ ፓርክ በቂ ጥበቃ እና እንክብካቤ እየተደረገለት ባለመሆኑ ጉዳት እየደረሰበት
እንደሚገኝ አሚኮ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ነግረውናል፡፡ ካነጋገርናቸው ነዋሪዎች መካከል አቶ ዓለምነው ደምለው
እንዳሉት በፓርኩ ውስጥ ለአስራ አምስት ዓመታት በእርሻ ሥራ ተሰማርተው ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጅ አካባቢው በፓርክነት ሲከለል
የእርሻ ሥራውን ማቆማቸውን ነግረውናል፡፡ በዚህ ወቅትም በፓርኩ ውስጥ የእርሻ ሥራ ቢቆምም አሁንም ግን ልቅ የእንስሳት
ግጦሽ፣ የዱር እንስሳት አደን፣ ሰደድ እሳት እና መሰል ችግሮች በፓርኩ ህልውና ላይ አደጋ መደቀናቸውን ነግረውናል።
የመንግሥት ክትትል እና ቁጥጥር ዝቅተኛ መሆኑንም አንስተዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ፈረደ ጫኔ እንዳሉት ደግሞ በሰኔ ወር ጀምሮ ቁጥጥር ስለሚደረግ እርሻውን ማስቆም ቢቻልም ልቅ
ግጦሽ፣ ስደድ አሳት እና አደንን ማስቆም አልተቻለም። በፓርኩ የተደራጀ መሰረተ ልማት ባለመሟላቱ የተመደቡ ሠራተኞች
ከከተማው በመመላለስ የጥበቃ ሥራ ማከናወናቸውን እንደ ችግር አንስተዋል፡፡ አካባቢው የተጠናከረ ጥበቃ እንዲደረግለት
በየጊዜው ጥያቄውን ለወረዳው ቢያቀርቡም መፍትሄ ማምጣት አልተቻለም፡፡ በፓርኩ መሠረተ ልማት በማሟላት ጥበቃው
መጠናከር እንደሚገባም መክረዋል።
የአማራ ክልል አካባቢ ደን እና ዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን የዱር እንስሳት ጥናትና ጥበቃ ዳይሬክተር አብርሃም
ማርየ እንዳሉት የጎደቤ ፓርክ የሰራሃ በርሃ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርገውን ግስጋሴ በመመከት ከሚታወቁ አልጣሽ፣ ማሕበረ
ሥላሴ፣ ሽመለጋራ፣ የአንገረብ እና የቃፍታ ሁመራ ፓርኮችና ማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት
ደኖቹ “አረንጓዴ ዘብ” በመባል ይጠራሉ። እነዚህ አካባቢዎች ከፍተኛ የሳር፣ ቁጥቋጦ እና የእጽዋት ሽፋን ያላቸው በመሆኑ
በክረምት ወቅት የአካባቢውን ሙቅት በመቀነስ አስተዋጽኦዋቸው የጎላ ነው።
ከደጋማው የሀገሪቱ ክፍል ተነስተው ወደ ቆላማው ክፍል የሚወርዱ ወንዞችን ውኃ በስፋት ስለሚጠቀሙ ለደን ሽፋኑ መስፋፋት
እንደ አንድ ምክንያት ተነስቷል። ከሱዳን ፀሐያማ ወቅት የሚመጣውን አስቸጋሪ አሸዋማ ነፋስ የመከላከል አቅም እንዳላቸውም
አንስተዋል።
የሰሃራ በርሃ ከሰሜን አፍሪካ እና ቻድ ተነስቶ ወደ ደቡብ እና ምሥራቅ አፍሪካ በተለይም ደግሞ ምዕራብ ሱዳንን ሲያጠቃ
በዓመት 100 ኪሎ ሜትር ፍጥነት ይስፋፋ እንደነበር ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡ እነዚህ ደኖች የበርሃማነቱን መስፋፋት ፍጥነት
ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርገውን ጉዞ ወደ 10 ኪሎ ሜትር ዝቅ እንዲል ማድረጋቸውን አንስተዋል። ደኖቹ (ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ)
በማመቅ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡
ጎደቤ ፓርክም በሄክታር እስከ 76 ቶን (ካርቦንዳይ ኦክሳይድ) የማመቅ አቅም አለው ተብሏል፡፡ ፓርኩ ወደ ካርቦን ገበያ መግባት
ቢቻል ደግሞ ከ5 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ገንዘብ በዓመት ያስገኛል፡፡
ይሁን እንጅ እስከ አሁን በኢትዮጵያ ለካርቦን የተከፈለው ብቸኛ ቦታ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ውስጥ በሚገኝ
2 ሺህ ሄክታር ደን በአንድ የጃፓን ኩባንያ መሆኑን ዳይሬክተሩ አንስተዋል። ደኖች ካርቦንን ከማመቅ ባለፈ የበርሃማነት መስፋፋትን
በመከላከል፣ የሥነ ምህዳር ውኃ የመያዝ አቅምን በማጎልበት፣ የመሬት መሸርሸርን በመከላከል፣ የዝናብን የተፈጥሮ ኡደት
ለማስቀጠል ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ሥራ እየሠራች እንደምትገኝ አቶ አብርሃም ጠቅሰዋል፡፡ የተፈጥሮ ደኖችን እና ብሔራዊ
ፓርኮችንም የመንከባከብ ሥራ እያከናወነች መሆኑን ነግረውናል፡፡
የጎደቤ ፓርክ ችግርን ለመቅረፍ ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ ጥበቃ እየተደረገ እንደሚገኝ አቶ አብርሃም ገልጸዋል፡፡ በዚህ ወቅትም 24
ስካውቶች ተመድበውለታል ብለዋል፡፡ ይሁን እንጅ በበጀት እጥረት እና በመሰረተ ልማት ችግር በታሰበው መጠን ክትትል እና
ቁጥጥር ማድረግ አለመቻሉን አንስተዋል፡፡ ማሕበረሰቡም አካባቢውን እንዲጥብቅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አቶ አብረሃም እንደገለጹት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ፓርኩ ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት ተደጋጋሚ እና ያልተሳኩ የበጀት
ጥያቄዎችን ለክልል ምክር ቤቱ እያቀረበ ነው፡፡ ከግበረ ሰናይ ድርጅቶችም በጀት ለማፈላለግ ያደረገው ጥረትም አልተሳካም፡፡
ወረዳዎችም ባላቸው አቅም ችግሮችን እንዲቀርፉ ቢጠየቁም ተገቢውን ትኩረት እየሠጡ አይደለም፡፡ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ
ችግሩ እንዲቀረፍ ጥረት እንደሚያደርግ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m