ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በድጋሜ የፊፋ ፕሬዝዳንት ኾነው ተመረጡ።
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ፕሬዝዳንት ኾነው በድጋሜ ተመርጠዋል።
የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) 73ኛው መደበኛ ስብስባውን የማኅበሩ አባል ሀገራት በተገኙበት በአፍሪካዊቷ ሀገር ሩዋንዳ ኪጋሊ ላይ እያደረገ ይገኛል።
ማህበሩ በዛሬው ዕለትም በሩዋንዳ ኪጋሊ በቀጠለው መደበኛ ስብስባው ከ 2023 እስከ 2027 ድረስ ፊፋን በኃላፊነት የሚያገለግል ፕሬዝዳንት መምረጡን አስታውቋል።
በ2016 የቀድሞ የፊፋ ፕሬዝዳንት ሴፍ ብላተርን ተክተው ወደኃላፊነት የመጡት የ52 አመቱ ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ዘንድሮ በእጩነት የቀረቡት ለሶስተኛ ጊዜ ነው።
በዚህ ዓመቱም ምርጫም ያለምንም ተቀናቃኝ ለሶስተኛ ጊዜ የተመረጡት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ለተጨማሪ አራት አመታት ተቋሙን የሚመሩ ይሆናል።
ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ከተመረጡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ “የፊፋ ፕሬዝዳንት መሆን የተለየ ትልቅ ክብር እና ትልቅ ኃላፊነት ነው ፣ ፊፋን እና ሁሉንም የፊፋ አባል ሀገራት ለማገልገል ቃል እገባለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ በአዲሱ የስልጣን ዘመናቸው አነስተኛ አቅም ላላቸው ሀገራት የቪዲዮ ረዳት ዳኝነት ስርዓትን (VAR) በጥቂት ካሜራዎች በመታገዝ ለመተግበር እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል።
ኢንፋንቲኖ በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ውስጥ እስከ 11 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማስገባት እቅድ መያዙን ይፋ ማድረጋችቸውን ፍራንስ 24 ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!