ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ)“ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን” በሚል መሪ መልእክት የከፍተኛና መካከለኛ አመራር ኮንፈረንስ በባሕር ዳር ተጀምሯል።
በኮንፈረንሱ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር ክቡር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ክልሉን መሪ በማሳጣትና የክልሉን ሕዝብ ሰላም በመናድ የሚመጣ ውጤት አይኖርም ብለዋል። አመራር በመግደል የአማራ ክልልን ችግር መፍታት አይቻልም ሲሉም ተናግረዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ አያይዘውም ለሕዝብ የገባናቸውን ቃሎች ቆጥረን ለመፈጸም ርብርብ ማድረግ ይገባል ያሉ ሲሆን በጽንፈኞች አጀንዳ እየተመራን ከልማት እና ከብልጽግና ጉዟችን ልንገታ አይገባም ብለዋል።
ያጋጠመን ችግር ውስብስብና አስቸጋሪ ነው ያሉት ዶክተር ይልቃል ይህንኑ በጥልቀት በመገምገም እና ለመፍትሔዎቹ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ኮንፈረንስ በማስፈለጉ ምክንያት መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ብልጽግና ፓርቲ የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች ለማስመለስ በሂደት ላይ ያለና ለተፈጻሚነቱ እየተጋ ያለ ፓርቲ መኾኑንም ገልጸዋል።
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ጋሻው አወቀ በበኩላቸው የአማራ ሕዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ በኾነ መልኩ ትግል ይደረጋል ብለዋል።
በክልሉ የገጠመንን ችግር በውል ተረድቶ ወደ ዕድል በመቀየር ከልሉን በብቃት የሚመራ ፓርቲ እና መንግሥት በመኖሩ ለዚሁ ዓላማ የሚታገል ቁርጠኛ አመራር እና አባል እንዲሁም ሕዝብን የሚያነሳሳ የሚዲያ እና ኮምዩኒኬሽን ሥራ ይሠራልም ሲሉ ዶክተር ጋሻው ተናግረዋል፡፡
ኮንፈረንሱ ለመላው የፓርቲው አመራር እና አባል በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለመ መኾኑን የተናገሩት ዶክተር ጋሻው ጠንካራ የፖለቲካ እሳቤና የተስተካከለ የፖለቲካ ትግል ማድረግ ይጠበቅታልም ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ከ1ሺህ 400 በላይ በክልሉ የሚገኙ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ተሳታፊ መኾናቸውም ተገልጿል።
ኮንፈረንሱ በቅርቡ ሕይወታቸውን ላጡት ለአቶ ግርማ የሽጥላ እና አብረዋቸው ለተሰዉ ወንድሞች የጧፍ ማብራት ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
ከዛሬ ሐሙስ ግንቦት 10/2015 ዓ/ም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት የሚካሄድ ኮንፈረንስ መኾኑም ተገልጿል።
ኮንፈረንሱ “ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን” በሚል መሪ መልእክት ይካሄዳል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!