ባሕርዳር: መጋቢት 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አልማ በዘጠና ቀናት ፕሮጄክት ከ1 ሺህ በላይ የትምህርት መማሪያ ሕንጻዎችን ገንብቶ ለተጠቃሚዎች እንደሚያስረክብ አስታውቋል።
የአማራ ልማት ማኅበር ( አልማ) በአማራ ክልል የልማት ፕሮጄክቶችን ለዓመታት ሲተገብር ቆይቷል። አሁንም በመተግበር ላይ ነው። የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) የማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮጄክቶችን በዘጠና ቀናት ለመተግበር እየሠራ ነው። የአልማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መላኩ ፋንታ በዘጠና ቀናት የሚተገበሩትን ፕሮጄክቶች አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው አልማ በዘጠና ቀናት ፕሮጄክቶቹ 1 ሺህ 832 የትምህርት መማሪያ ሕንጻዎችን አጠናቅቆ ለተጠቃሚዎች ያሰረክባል ብለዋል። የትምህርት መማሪያ ሕንጻዎች በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች የሚተገበሩ ናቸው።
አልማ በትምህርት፣ በጤና እና በሥራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም ነው የተናገሩት። ‘የራሳችንን ችግር በራሳችን መፍታት አለብን’ በሚል እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል። አልማ የማኅበረሰብ ተሳተፎ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ያለ ተቋም መሆኑንም አስታውቀዋል።አልማ የሕዝብ ተቋም የሆነና በሕዝብ ውስጥ ያለ ተቋም እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት።
አልማ በሠላሳ ዓመታት ውስጥ እያደገ እና የልማት አጋር ሆኖ የመጣ ተቋም መሆኑንም ተናግረዋል። ተቋሙ በያዘው እቅድ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ1 ሺህ 700 በላይ ትምህርት ቤቶችን ገንብቶ ለሕዝብ አስረክቧል ብለዋል። አልማ ታላቅ የልማት አጋር ሆኖ እየሠራ ስለመኾኑም ገልጸዋል። አልማ ከ2015 ዓ.ም እስከ 2017 ዓ.ም የሚቆይ ስትራቴጂክ እቅድ እንዳለውም ተናግረዋል። የማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮጄክት መተግበር አዋጭ ነው ያሉት አቶ መላኩ ፕሮጄክቶቹ በሕዝብ ተሳትፎ የሚፈጸሙ መሆናቸውን ነው ያብራሩት።
በዘጠና ቀናት በሚተገበሩት ፕሮጄክቶች ለ90 ሺህ ወጣቶች የሥራ እድል ይፈጠርላቸዋል ብለዋል። ለፕሮጄክቱ ማስፈጸሚያ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧልም ነው ያሉት። ፕሮጄክቶቹ ተለይተው ወደ ሥራ እየገቡ መሆናቸውንም ገልጸዋል። በማኅበረሰብ ተሳትፎ የሚሠሩ ፕሮጄክቶች ወጪ ቆጣቢ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
ታላቅ ዓላማ ላላቸው ፕሮጀክቶች ባለሀብቶች፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ሚዲያ እና ሌሎች አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። ሥራውን አሳክተን የመማሪያ ክፍል ጥበትን ትርጉም ባለው መንገድ እንቀንሳለንም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!