ባሕር ዳር: ጥቅምት 29/2013 ዓ.ም (አብመድ) ለአንድ ቀን የተካሄደው የአማራ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር፣ 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ጉባኤ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መክሮ፣ የውሳኔ ሃሳብ አስቀምጦ እና የርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገርን ሹመት አፅድቆ ተጠናቋል፡፡
ርእሰ መሥተዳደሩ በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ ከፈፀሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር ክልሉ የልማት ቀጠና እንዲሆን በትኩረት እንሰራለን ብለዋል፡፡
ክልሉ ባለፉት ዓመታት የሰላም እና የፀጥታ ችግሮች ፈትነውት ነበር ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ አሁን እየታየ ያለውን የሰላም ተስፋ በማስፋት ለኢንቨስትመንት የተመቸ ክልል እንዲሆን በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት፡፡
በአሁኑ ወቅት የክልሉን የፀጥታ ሃይል የሚፈትን የታጠቀ ፀረ-ሰላም ኃይል አለመኖሩን ጠቁመው በቅርቡ ከሃዲው ትህነግ በክልሉ የድንበር አካባቢ ጥቃት በመፈፀም ወደ አስገዳጅ ጦርነት እንድንገባ ተደርገናል ብለዋል።
ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የአማራ ህዝብ የተለያዩ ቅፅል ስሞችን በመስጠት እንዲገለልና የጥቃት ሰለባ እንዲሆን ሲሰራ የቆየው ከሃዲው ትህነግ ትዕግስታችን ሲያበሳጨው ግልፅ ጥቃት ሰንዝሮብናል ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳደሩ በንግግራቸው፡፡ ራሱ በጀመረው ትንኮሳ ግብዓተ መሬቱ ተቃርቧል ያሉት ርእሰ መሥተዳደር አገኘሁ ተሻገር የተጀመረው የግዳጅ ጦርነት በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ መላው የሃገሪቱ ህዝብ ከመንግሰት ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
በሃገርም ሆነ በክልል ደረጃ ፈታኝ ሁኔታዎች መኖራቸውን ያወሱት አቶ አገኘሁ ችግሩ በማያዳግም ሁኔታ እንዲጠናቀቅ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ወቅታዊ ሁኔታውን ለማረም ከሚሰራው ተልዕኮ ጎን ለጎን የክልሉ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው የግብርና ልማት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
በከተሞች የሚስተዋለውን የመሰረተ ልማት አቅርቦት እጥረት፣ ህገ ወጥነትን በመከላከል፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል፣ በኢንቨስትመንት ዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን መፍታት፣ ባለሃብቱ በተሰማራበት ምጣኔ ሃብታዊ ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፍ ማድረግ እና የስራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት እንደሚደረግም አስገንዝበዋል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ተቋረጦ የነበረው የመማር ማስማር ስራ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ተፈፃሚ ይደረጋል ያሉት አቶ አገኘሁ የሚስተዋለውን የመማሪያ ክፍል ጥበትም ባለሃብቱንና የልማት ድርጅቶችን በማሳተፍ እንዲፈታ ይደረጋል ብለዋል።
“አሁን ያለንበት ወቅት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የአማራ ህዝቦችን አንድነት የሚጠይቅ ነው” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለክልሉ ልማትና እድገት በጋራ እንዲቆሙም ጠይቀዋል።
የክልሉን ሰላም፣ ልማት እና እድገት ለማረጋገጥ የመላው ህዝብ የላቀ ተሳትፎ ወሳኝ ነው። የሚጠቅመንን ሃሳብ ሁሉ ከየትኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ለመቀበል ዝግጁ መሆናችንን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው