“አሁን ላይ በጠንካራ ሥራ ያመጣነውን ሰላም አጠናክረን በመቀጠል የሕዝባችንን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትጋት መሥራት አለብን” የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)

0
112
Made with LogoLicious Add Your Logo App
ጎንደር: ሕዳር 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶር) እና ምክትል ርእሰ መስተዳድር ጌታቸው ጀምበር (ዶ/ር)ን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች በተገኙበት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ያለመ የምክክር መድረክ በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው።
የአማራ ሕዝብ ከውስጥና ከውጭ በሚሰነዘሩ ሴራዎች ብዙ ፈተናዎች ተጋርጠውበት ቆይተዋል ያሉት የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ጫናዎችን የምንቋቋመው ውስጣዊ አንድነታችንን ስናጠናክር መሆኑን በተግባር አይተናል ብለዋል።
የውስጥ ሰላማችንን ከፈተኑን አንዱ በጎንደርና አካባቢው የነበረው የሰላም እጦት እንደነበር ያስታወሱት ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) የሰዎች እንቅስቃሴ ከመገደብ ጀምሮ ሕገወጥ እንቅስቃሴዎች ጎልተው እንደነበር ነው የገለጹት።
Made with LogoLicious Add Your Logo App
አማራና ቅማንት አንድ መዓድ የሚቋደሱ፤ በማኅበራዊ ትስስር የተቃኙ ሁነው ሳለ ወደ ግጭት እንዲገቡ የተደረገበት ሴራ ብዙ ዋጋ አስከፍሎን ቆይቷል ነው ያሉት።
ሰላም በማጣታችን ያተረፈ ማንም ሕዝብ የለም፤ ምናልባት ከሕዝብ ግጭት የሚያተርፉት የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን ብቻ ናቸው ብለዋል።
የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሰላም አማካሪ ምክር ቤት ተቋቁሞ ሰፊ ጥረት ተደርጎ አሁን ላይ ለደረስንበት ሰላም አድርሶናል ነው ያሉት።
አማካሪ ምክር ቤቱ ሕዝብን ወደ አንድ ለማምጣት ላከናወነው ወደር የሌለው ሥራ የክልሉ መንግሥት ትልቅ ክብር አለው ሲሉም ምስጋና አቅርበዋል።
በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ወደ ቀያቸው ሲመለሱ ያሳዩት ፍቅርና መተሳሰብ በአንድነት ከመኖር ውጭ ሌላ ምርጫ እንደሌለ በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል ርእሰ መስተዳድሩ።
በዚህ ሥራ ከጎንደር እስከ መተማ ያለው መስመር ያለምንም ስጋት እንቅስቃሴ የሚደረግበት ቀጣና ሆኗል፤ ይህም የአካባቢውን የግብርና ምርት ውጤታማነት ለማሳደግ ጉልህ ድርሻ ተወጥቷል፤ በመኸር እርሻ የታዬው የሰብል ልማት የመጣው ሰላም በመኖሩ ሰለሆነ ይህንን ተግባራችንን አጠናክረን በመቀጠል የሕዝቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትጋት መሥራት አለብን ነው ያሉት።
ሰላም በማጣታችን ብዙ ተጎድተናል፤ ወገኖቻችን ተፈናቅለዋል፤ ከዚህ ተምረን ለሰላም ዘብ በመቆም ውስጣዊ አንድነታችንን አጠናክረን የጠላትን ዓላማ ማክሸፍ ይኖርብናል ሲሉም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:–ስማቸው እሸቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!