“ንጉሷን የምታወሳው፤ እሴቷን የማትረሳው ከተማ”

335

እንጅባራ: ሕዳር 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አቀማመጧ ከደጋው ለመጡ መናፈሻ፤ ከበርሃው ለሚመጡት መተንፈሻ ነው፡፡ ውብ አየር፣ ማራኪ መልካ ምድር፣ የሰጡትን አብቃይ መሬት፣ እንግዳ ተቀባይ ባለቤት ሕዝብ ሰፍሮባታል፡፡ የማይለምድ እንስሳት የማይበቅል እጽዋት በአካባቢው የለም ይባላል፡፡ የደገኞቹ በጋ፤ የበርኽኞቹ ወይና ደጋ የሆነችው ሽቅርቅር ከተማ የምሸት ድምቀቷ የቀን ውበቷ አጃአይብ የሚያሰኝ ግሩም እና ተወዳጅ ነው፡፡

የበርኸኞቹ ገነት፣ የደገኞቹ ሙቀት እና የነዋሪዎቿ ሰገነት የሆነችው ከተማ እድሜ ጠገብ የምትባል ናት፡፡ 1939 ዓ.ም እንደተቆረቆረች ይነገርላታል፤ ከ1941 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በማዘጋጃ ቤት ትመራ እንደነበር ድርሳናት ያሳያሉ፡፡ ስልጡን እና ቀደምት፤ ብዝሃ እና ሕብረ ብሔራዊት ከተማ ነች፡፡ የቀደመ ስያሜዋ “ቀ. ኃ. ሥ በር” ይባል ነበር አሉ፡፡ ቀዳሚ ስያሜዋ ታሪካዊ የአሁኑ ስያሜዋም ደግሞ ተምኔታዊ የሆነች ደማቅ እና ምስጥራዊ ከተማ ናት፡፡

የመጨረሻው ዘውዳዊ ንጉስ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ከጀኔቫው የሊግ ኦፍ ኔሽን አቤቱታ መልስ በሱዳን በኩል ወደ ሀገራቸው ሲገቡ ድንኳናቸውን ተክለውባታል፤ ልዑካቸውን አሳርፈውባታል ይባላል፡፡ ይህን የንጉሱን ታሪካዊ ጉዞ ተከትሎም እረፍት ባደረጉበት አካባቢ የተቆረቆረችው ከተማ የመጀመሪያ ስያሜዋ ቀ. ኃ. ሥ በር ይባል ነበር አሉ፡፡ ከተማዋ ለዘመናት የንጉሷን ዱካ ያከበረች፤ ታሪካዊ አሻራቸውን የዘከረች ኢትዮጵያዊ ድልድይ እና ድርሳን የሆነች ከተማ ነች፡፡

በሰንበሌጥ ሳር የለመለመችው እና በሦስት ወንዞች የተከበበችው ታሪካዊት መናገሻ ከተማ የአሁኑን መጠሪያዋንም ያገኘቸው በምክንያት ነው ይባልላታል፡፡ በአዊኛ ቋንቋ “ቻ” ማለት “ነገ” ማለት ሲሆን “ግኒ” ማለት ደግሞ “ቤት” ማለት ነው አሉ፡፡ “የነገ ቤቴ” ሲሉም “ቻግኒ” የሚል መጠሪያ ሰጧት፡፡ ቻግኒ ታሪኳን በሚገባ የዘከረች፤ ትናንትናዋን ያሳመረች እና ነገዋንም ቀድማ የተለመች ከተማ ነችና “የነገ ቤቴ” ሲሉ ቻግኒ የሚል ምስጢራዊ እና እረቂቅ ስያሜ ቸሯት፡፡

ቻግኒ ከሱዳን ድንበር በቅርብ እርቀት የምትገኝ ከተማ ስትሆን የከተማዋ ነዋሪ ስብጥርም ብዝሃነት ጎልቶ የሚስተዋልበት ነው፡፡ ቻግኒ የሃይማኖት ብዝሃነት እና አብሮነት ምሳሌም ናት፡፡ አዛን በዝሁር፤ ማሕሌት በሌሊት የሚዘወተርባት ከተማ የምሽት ዓለማዊ ሙዚቃዎቿም ጉራማይሌ የሚባልላቸው ናቸው፡፡

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ እና የጃዊ ሕብር ስኳር ፍብሪካ መሸጋገሪያ የሆነችው ቻግኒ የዶንዶር እና የጋርቾ ፏፏቴዎች፤ የሞሶቦ እና ጓንጓያ ሰንሰለታማ ተራሮች፤ የስሌማን ዋርካ እና ቀደምት የሃይማኖት ተቋማት የመስህብ ሃብቶቿ ናቸው፡፡ ቻግኒ የመጻዒዋ ኢትዮጵያ ምልክት እና የታሪካዊቷ ኢትዮጵያ ምሳሌ የሆነች መሸጋገሪያ ከተማ ናት፡፡

የአብሮነት እሴቷን ጠብቃ የዘለቀችው ቻግኒ በከተማዋ እምብርት ላይ ቀ.ኃ.ሥ በር የሚል ሆቴል ሳይ ትናንቷን የማትረሳ ከተማ ለማለት ተገደድኩ፡፡ “ንጉሷን የምታወሳው፤ እሴቷን የማትረሳው ከተማ” በቅርቡ ደግሞ “የነገ ቤቴ” በሚል የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ሌላ ታሪክ ሰርታለች፡፡ ስለዚህ ዘመቻ እና ውጤቱም ከሰሞኑ አሚኮ ድንቅ ዘገባ ያስቃኛችኋል፡፡

በታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J