ኅብረተሰቡ አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችን በመጠቀም ቤት የመገንባት ልምዱን እንዲያዳብር የፈጠራ ባለሙያዎች ጠየቁ፡፡

0
25
ኅብረተሰቡ አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችን በመጠቀም ቤት የመገንባት ልምዱን እንዲያዳብር የፈጠራ ባለሙያዎች ጠየቁ፡፡
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርም የፈጠራ ባለሙያዎችን በማበረታታት ዘርፉን ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን ገልጿል፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 05/2013 ዓ.ም (አብመድ) የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ለኮንስትራክሽን ቴክኖሎጅ እውቅና ለመስጠትና ለማበረታታት ምክክርና አውደርዕይ እያካሄደ ነው፡፡ በምክክር መድረኩ እና አውደርዕዩ ላይ የፈጠራ ባለሙያዎች፣ አምራቾችና አስመጭ ድርጅቶች እየተሳተፉ ነው፡፡
የቤዛዊት ሽኔል ሆም ተገጣጣሚ ህንፃ ማምረቻ ፋብሪካ በተለመደው መንገድ የግድግዳ ኮለን ማቆም ሳያስፈልግ፣ እንጨትና ጭቃ ሳንጠቀም ከፋብሪካ የተሰራውን ጥሬ እቃ በመጠቀም ቤት መሥራት የሚያስችል ጥሬ እቃ በአውደርዕዩ አቅርቧል፡፡
በፋብሪካው የምርት ክፍል ባለሙያ ወጣት ሠውነት አዝመራው ጥሬ እቃው ለማንኛውም አይነት ግንባታ የሚያገለግል ሲሆን በተለምዶ ግንባታ የሚወስደውን ጊዜ ከ40 እስከ 50 በመቶ እንደሚቀንስ ተናግሯል፡፡ በወጭ ደረጃም 31 ነጥብ 2 በመቶ ባነሰ ገንዘብ ሰርቶ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ገልጿል፡፡ እንደ ባለሙያው ማብራሪያ በፋብሪካው የሚመረተው ጥሬ እቃ አንድ ጊዜ ከተመረተ በኋላ ለሚፈለግበት ቦታ ካልተስማማ ተመልሶ ወደ ፋብሪካ ገብቶ በአዲስ መመረቱ ልዩ ያደርገዋል፤ ምርቱ እውቅና ተሰጥቶት በማኅበረሰቡ ዘንድ ተፈላጊነቱ ቢጨምርም አሁንም ነባሩን አሰራር ለማስቀጠል የሚታየው ፍላጎት ፈተና ሆኖባቸዋል፤ ፋብሪካው ለደረጃ፣ ለግድግዳ፣ ለወለወልና ጣራ የሚያገለግል ጥሬ እቃ እያመረተ ነው፡፡
ማኅበረሰቡ ከተለመደው አሠራር ወጥቶ አዲስ የግንባታ ፈጠራ ውጤቶችን እንዲጠቀም መንግሥትም ዘርፉን በተሻለ መንገድ በመደገፍ የሚታየውን የጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ ድጋፍ እንዲያደርግ ባለሙያው መልዕክት አስተላልፏል፡፡
አቶ ብርሃኑ ካሳ የሎዛና ብርሃኑ የተገጣጣሚ ቤቶች ድርጅት ባለቤት ናቸው፡፡ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ባዘጋጀው የምክክር መድረክና አውደርዕይ ተሳታፊ ናቸው፡፡ እንደ አቶ ብርሃኑ ገለጻ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ የልምድ ልውውጦች እና አውደርዕዮች የግንባታ ፈጠራ ሥራዎችን በማስተዋወቅ ረገድ ድርሻቸው የጎላ ነው፡፡ የፈጠራ ሥራቸው 20 ዓመት ጥናት የተደረገበት መሆኑንና የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከሌሎች ባለድርሻ አካት ጋር በመተባበር 3 ዓመታትን ጥናት በማድረግ እውቅና ሰጥቷቸዋል፡፡
በርካታ የፈጠራ ባለሙያዎች ገበያውን እየተቀላቀሉ በመሆኑ ለሀገር በቀል የፈጠራ ሥራ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ብርሃኑ ገለጻ በድርጅታቸው የሚሰራው ቤት በቃጫና በኮንክሪት የሚሠራ ሲሆን አስተማማኝና ጥራቱን የጠበቀ ነው፡፡ ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ አንድ ቤት ሰርቶ ማጠናቀቅ እንደሚቻል አቶ ብርሃኑ ነግረውናል፡፡
ማኅበረሰቡ በቀላሉ የቤት ባለቤት ለመሆን ምርታቸውን እንዲጠቀምም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ በቃጫና በኮንክሪት የሚሰራው ቤት የውጭ ምንዛሬን ከማስቀረቱ በተጨማሪ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡ ለመንግሥትም ገቢን በማሳደግ በኩል ድርሻው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ቃጫ በማምረት ሥራ ለተሰማሩ ሰዎች ገቢ በማስገኘት በኩል ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው የፈጠራ ባለሙያው አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡ በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ መስፍን አሰፋ (ዶክተር) በሀገሪቱ የሚታየውን የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጅ እጥረት ለመፍታት መሰል ምክክርና አውደርዕይ የጎላ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ የኮንስትራክሽን ዘርፉን ተመራጭና ተወዳዳሪ ለማድረግ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በኮንስትራክሽን ዘርፉ ግብዓት አንዱ ማነቆ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው እነዚህን ችግሮች በሀገር ውስጥ የፈጠራ ሥራዎች መተካት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ በኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚታየውን የጥራትና የተወዳዳሪነት ችግር ለመፍታት የቤተሙከራ ውጤቶችን መጠቀም ተገቢ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ እንደ ዶክተር መስፍን ማብራሪያ በሀገራችን በርካታ ሰዎች አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን እያስተዋወቁ ነው፤ እውቅናም ተሰጥቷቸዋል፤ እነዚህን የፈጠራ ውጤቶች ወደ ሥራ በማስገባት ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
በተጨማሪ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት ይቻላል ብለዋል፡፡ የፈጠራ ሥራዎች ለወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር በኩልም የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ የጎላ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡
በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮች ወደ ተግባር የሚገቡበት መንገድም ይመቻቻል ብለዋል ሚኒስቴር ዴኤታው፡፡
የካቲት 03/2013 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ክልል ምክር ቤት አዳራሽ የተከፈተው የኮንስትራክሽን ፈጠራ ውጤቶች አውደርዕይ በበርካታ ሰዎች እየተጎበኘ ነው፡፡ አውደርዕዩ እስከ የካቲት 08/2013 ዓ.ም እንደሚቆይ እና ማንኛውም ሰው እንዲጎበኝ ጥሪ ተላልፏል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here