ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 6/2012 ዓ.ም (አብመድ) በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽሕፈት ቤት የተገነባውን ትምህርት ቤት ማኅበረሰቡ እንዲንከባከበው የክልሉ ትምህርት ቢሮ አሳሰበ፡፡
በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽሕፈት ቤት አማካኝነት የተገነባው የሎዛ ብርሃን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዛሬ ሲመረቅ በሥነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፋለ ‹‹በክልሉ የትምህርት ተደራሽነት እና ሽፋንን ለማሳደግ ብዙ ርቀት ቢኬድም ከሚፈለገው ደረጃ አልተደረሰም›› ብለዋል፡፡
ምንም እንኳን አማራ ክልል በሕዝብ ብዛቱ በሀገሪቱ በሁለተኛ ደረጃ የሚገኝ ቢሆንም በሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ሽፋኑ በ3ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በመሆኑም ‹‹ቀጣይ በርካታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መገንባት ያስፈልጋል›› ብለዋል ቢሮ ኃላፊው።
በተለይም አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ ሲደርግ ብዙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚያስፈልጉ ያመለከቱት ኃላፊው ‹‹ኅብረተሰቡንና ለጋሽ ድርጅቶችን በማሳተፍ ተጨማሪ ትምህርት ቤቶችን መሥራት ያስፈልጋል›› ብለዋል።
የትምህርት መስፋፋት ድህነትን ከመሠረቱ ለመቅረፍ ትልቅ ስንቅ መሆኑን ያስታወሱት ኃላፊው ተማሪዎች ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ተገንዝበውና ተምረው ብቁ እንዲሆኑ የትምህርት ቤቱ ግንባታ የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው አመልክተዋል።
መምህራን ጠንክረው እንዲያስተምሩና ክልሉን ብሎም ሀገሪቱን የሚያስጠራ ተማሪ እንዲያፈሩ ዶክተር ይልቃል መክረዋል። ተማሪዎችም ትምህርት ቤቱን እንዲንከባከቡ አሳስበዋል። ሠላም ከምንም በላይ አስፈላጊ በመሆኑ ተማሪዎችም ሆኑ ወላጆች ቅድሚያ ለሠላም እንዲሰጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዶክተር ይልቃል ለቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤትና የግንባታ ሠራተኞች ችግሮችን ተቋቁመው በመሥራታቸውም ምስጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ