ትኩረት የሚሻው የተፈናቃዮች ሁኔታ።

111
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ

ሰቆጣ: መጋቢት 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) እሙሐይ አበዙ ሰንበት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አበርገሌ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። እሙሐይ አበዙ አሸባሪው ቡድን በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ ባደረሰው ማኅበራዊ ቀውስ አንዲት ልጃቸውን ይዘው አጋዥ ፍለጋ ለቀናት ያሕል ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጠው ወደ ሰቆጣ ከተማ ተፈናቀሉ። ከዚህ በፊት በአካባቢው ማኅበረሰብ ይደገፉ እንደነበር ያነሱት እሙሐይ አበዙ የማኅበረሰቡ ሀብትና ንብረት በሽብር ቡድኑ በመዘረፉ የተነሳ የሚቀመስ ጠፋ። በዚህ ጊዜ እሙሐይ አበዙ በሰቆጣ ከተማ አስተዳደር “ሚንዲኪሩ” መጠለያ ጣብያ መቀላቀላቸው ግድ ኾነ። እሙሐይ አበዙ እንዳሉት ከነበረባቸው ችግር አኳያ በመጠለያ ጣብያው ቢቀላቀሉም አኹንም ግን የተፈለገውን ያህል ድጋፍ እየተደረገላቸው አለመኾኑን ነው የነገሩን።

ወይዘሮ አዲስ አምቤ እንደነገሩን ደግሞ በአበርገሌ ወረዳ ጠላ በመጥመቅ፣ ባለቤታቸው ደግሞ የቀን ሥራ በመሥራት አራት የቤተሰብ አባላትን ያስተዳድሩ ነበር። ይሁን እንጂ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በአካባቢው ወረራ ከፈጸመ ጀምሮ ይሠሩ የነበሩት ሥራ ቆመ።

የአካባቢው ማኅበረሰብ ሀብትና ንብረት በመዘረፉ ማኅበረሰቡም ለችግር ተጋለጠ። በዚህም ምክንያት የሚበላ ነገር በመጥፋቱ ወደ መጠለያ ጣብያ ለመቀላቀል ተገደዱ። በመጠለያ ጣብያ መኖር ከጀመሩ አንድ ወር እንደኾናቸው የገለጹት ወይዘሮ አዲስ በአንድ አዳራሽ የሚኖረው ተፈናቃይ ቁጥር ከፍተኛ በመኾኑ ለጉንፋን እና ለሆድ ሕመም መጋለጣቸውን ገልጸውልናል። በመንግሥት የሚደረገው ድጋፍም ዝቅተኛ በመኾኑ ችግር ላይ መውደቃቸውን ነው የነገሩን።

አቶ በላይ መንግሥቴም በተፈጸመባቸው ግፍ ከቀያቸው ተፈናቅለው ለስምንት ወራት ያኽል በመጠለያ ጣብያ እንዲጠለሉ ተገደዋል። የሚደረገው ድጋፍም ዝቅተኛ በመኾኑ ችግሩ አለመቀረፉን አንስተዋል። በአንድ አዳራሽ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተፈናቃይ መኖሩ ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ መኾናቸውን አንስተው ችግሩ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ ወይዘሮ ዝናሽ ወርቁ እንዳሉት የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን በብሔረሰብ አስተዳደሩ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የምግብ ድጋፍ እና የመጠለያ ግንባታ ሥራ እያከናወነ ይገኛል። ይኹን እንጂ የተፈናቃዩ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ድጋፉ በቂ አለመኾኑን ነው ቡድን መሪዋ የነገሩን። በዚህም ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡር እናቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ይበልጥ የችግሩ ሰለባ ኾነዋል።

በአንድ መጠለያ ጣብያ ከ10 ሺህ በላይ ሕዝብ እንደመኖሩ ለእከክ፣ ተቅማጥ እና መሰል ከንጽህና ጉድለት ጋር ተያይዞ በሚመጡ በሽታዎች ተጠቂ መኾናቸውን ገልጸውልናል።

መንግሥት ከሚያደርገው ድጋፍ ባለፈ አንዳንድ ረጂ ድርጅቶች የቁሳቁስ ድጋፍ እያደረጉ እንደኾነም ነው ወይዘሮ ዝናሽ የገለጹት። በየቀኑ ከ2 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ወደ አካባቢው እንደሚገቡ ያነሱት ወይዘሮ ዝናሽ ችግሩን ለመፍታት ሌሎች ረጂ ድርጅቶችም ጥናት ከማድረግ ባለፈ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ባለሀብቶች እና ሌሎች ኢትዮጵያውያንም የተለመደውን ትብብራቸውን እንዲያሳዩ ጠይቀዋል። በተለይም የአልሚ ምግቦች፣ የመጠለያ፣ የውኃ፣ የመድኃኒት አቅርቦት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች በመኾናቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት ደግሞ መንግሥት የአካባቢውን ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

አቅም ያላቸው ነዋሪዎች ለቀናት ያህል ተጉዘው መጠለያ ጣብያ ቢደርሱም መምጣት ያልቻሉ አቅመ ደካሞች የከፋ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ አንስተዋል።

በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከ53 ሺህ 400 በላይ ተፈናቃዮች በአራት መጠለያ ጣብያዎች ይገኛሉ። በሰቆጣ ከተማ አስተዳደር “ሚንዲኪሩ” የመጠለያ ጣብያ ብቻ ከ2 ሺህ በላይ አባዎራዎች፣ በቤተሰብ ደረጃ ደግሞ 10 ሺህ የሚኾኑ ተፈናቃዮች በአንድ አዳራሽ ውስጥ ይገኛሉ።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/