ትናንት አሸባሪውና ወራሪውን ትህነግ ለማስወገድ የአማራው ደም ደሜ ነው፤ የኦሮሞው ደም ደሜ ነው ብለን ነበር። ዛሬ ደግሞ ይህን በተግባር ያስመሰከርንበት ነው” የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦቢኤን) ዋና ሥራ አስኪያጅ

0
103

መስከረም 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚዎችና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን በደቡብ ጎንደርና በሰሜን ወሎ ዞኖች ያወደመውን እና የዘረፈውን ንብረት ተመልክተዋል።

የኦሮሞ ብሮድካስት ኔትወርክ (ኦቢኤን) ዋና ሥራ አስኪያጅ ዝናቡ አስራት በምልከታቸው ላይ እንዳሉት ንጹሐን የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የተፈጸመው ተግባር ልብ የሚነካና ከሰው ልጅ የማይጠበቅ ነው። አሸባሪ ቡድኑ መጠነ ሠፊ ቁሳዊና ሰብዓዊ ውድመትን መፈጸሙን ተመልክተናል ነው ያሉት።

ይሁን እንጂ የአካባቢው ማኅበረሰብ ለሕልውና ዘመቻው እያደረገ የሚገኘው ድጋፍ የኢትዮጵያዊነትን ጨዋነትና አንድነት ያሳየ ነው ብለዋል።

ዋና ሥራ አስኪያጁ የሚዲያ የሥራ ኀላፊዎች ግንባር ድረስ መምጣታቸው እውነተኛውን ታሪክ በመረዳት በየግንባሩ የሚሠሩ ጋዜጠኞችን ለመደገፍ እንደሚጠቅምም ነው ያስረዱት።

“ትናንት አሸባሪውና ወራሪውን ትህነግን ለማስወገድ የአማራው ደም ደሜ ነው፤ የኦሮሞው ደም ደሜ ነው ብለን ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ይህንን በተግባር ያስመሰከርንበት ነው” ብለዋል። በዛሬው ምልከታቸውም ጠላትን ለመደምሰስ ከጫፍ እስከ ጫፍ የሚደረገውን ርብርብ ለማየት መቻላቸውን ነው የጠቆሙት።

ዋና ሥራ አስኪያጁ የሚዲያ አመራሩም ሆነ ባለሙያዎች በዚህ ትግል አስፈላጊውን መስዋእትነት መክፈል እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

የውጪ ሚዲያዎች የሚዘግቡት የሐሰት ዘገባ ትክክል አለመሆኑን የሀገራችን ሚዲያዎች ናቸው ማሳየት የሚጠበቅባቸው ብለዋል።

የደቡብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ብሩክ ሀብቴ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የምንሰማውን የቡድኑን አረመኔያዊ ተግባር ዛሬ በዓይናችን አይተናል ብለዋል። የሚዲያ የሥራ ኀላፊዎች ግንባር ድረስ በመገኘት መመልከታቸው ለወደፊት የበለጠ ሕይወት ያለው ሥራ ለመሥራት ያስችላል ነው ያሉት።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው “የአረመኔውን ተግባር በሚዲያ ከምንሰማው በላይ ነው ያየነው” ብለዋል። ሕዝቡ ለሕልውና ዘማቾች የሚያደርገው ድጋፍም ከሚጠብቁት በላይ እንደሆነ ተናግረዋል። ሁሉም የሚዲያ የሥራ ኀላፊዎች ባደረጉት ምልከታ በተደረገው ጦርነት የሽብር ቡድኑ ሲሸነፍ እያደረሰ ያለው ሰባዊ እና ቁሳዊ ውድመት መጠነ ሰፊ መሆኑንና ይህን ቡድን እንዳይመለስ አድርጎ ማጥፋት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡

ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ-ከፍላቂት

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m