“ትምህርት ቤቱ ሰራዊቱ ለሕዝቡ ቋሚ ሀውልት ያስቀመጠበት ነው።” ጀነራል አደም መሀመድ (የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም)

0
311

በኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የምዕራብ ዕዝ በደቡብ ጎንደር ዞን ክምር ድንጋይ ከተማ ያስገነባውን የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዛሬ አስመርቋል፡፡

በ”ጉና ቤጌምድር 2ኛ ደረጃ ትምርት ቤት” የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የታደሙት የምዕራብ ዕዝ መከላከያ ሰራዊት አዛዥ ሜጀር ጀነራል መሠለ መሠረት ሰራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነት ከመጠበቅ ባሻገር የሕዝብን ችግሮች የሚቀርፉ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ለአብነትም በመስኖ ልማት፣ በችግኝ ተከላ እና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ ጠቅሰዋል። ለሕዳሴው ግድብም ከ999 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዥ መፈጸማቸውን ገልፀዋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል አደም መሀመድ እንደተናገሩት ሰራዊቱ ለሀገር ውስጣዊ አንድነት መጠበቅና ለሉዓላዊነቷ እየሠራ ነው። ትምህርት ቤቱ ሰራዊቱ ቋሚ ሀውልት ለሕዝቡ ያስቀመጠበት እንደሆነም ጀነራል አደም ገልፀዋል።

ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ትምህርት ቤቱ በ10 ወራት እንደተጠናቀቀ ታውቋል። ስምንት ሕንፃዎችና 40 የመማሪያ ክፍሎች እንዳሉትም ተገልጧል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ በበኩላቸው ሰራዊቱ ላደረገው አስተዋጽዖ አመሥግነዋል። የሀገርን ዳር ድንበር ከማስከበር ባለፈ በማኅበራዊ አገልግሎትና በተቋማት ግንባታ እያደረገው ያለው ተግባር የሚያስመሰግን መሆኑንም ተናግረዋል።

በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ በሱዳን የገዳሪፍ ግዛት የሁለተኛ ክፍለ ጦር አዛዥን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ታድመዋል፡፡

ስምንተኛው የኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ቀን “የሀገራችንን ሉዓላዊነትና የሕዝባችንን ሰላም በጽናት እንጠብቃለን” በሚል መሪ መልዕክት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል። በዓሉ በጉና በጌምድር ወረዳ ክምር ድንጋይ ከተማም ከትምህርት ቤቱ ምረቃ ጎን ለጎን ተከብሯል።

ዘጋቢ፦ አዲሱ ተስፋዬ