ታሪክ ሕያው ምስክር ነው!

33

ባሕር ዳር ፡ ግንቦት 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ይህ ቀን እንዲመጣ አንዲት ሀገር በዓለም ሀገራት ጉባኤ ዘንድ ብቻዋን ቆማ ነጻነትን ዘምራለች፤ ስለፍትሕ ሞግታለች፡፡ የአፍሪካዊያን የነጻነት ቀን እውን ይሆን ዘንድ ከጦር ሜዳ ገድል እስከ ዲፕሎማሲ ትግል ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሏል፡፡

አፍሪካዊያን የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው የመወሰንም፤ የመበየንም አቅም አላቸው የሚለውን ሃቅ ፤ ቅኝ ገዥዎቹ እየመረራቸውም ቢኾን እንዲውጡት ለማድረግ ብዙ ውጣ ውረድ ተከፍሎበታል፡፡

ኢትዮጵያ ፍትህ በተጓደለበት፤ ባርነት በሰፈነበት የጨለማ ዘመን የነጻነት ፋና ወጊ ቀንዲል ኾና ታይታለች፡፡ ኢትዮጵያ በባርነት ወቅያኖስ ውስጥ ለሰጠሙት ጥቁር አፍሪካዊያን የነጻነት መርከብ ኾና አገልግላለች፡፡

ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛትን ሰንሰለት የበጣጠሰች የነጻዋ አህጉር ምስረታ መልህቅ ማረፊያ ወደብ ኾና ተገኘች፡፡ የማንዴላ መሰልጠኛ፤ የሙጋቤ መማጸኛ ከተማቸው ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሴኩቱሬ፤ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት አዳራሽ ነሬሬ ስለአህጉራዊ ነጻነት በነጻነት መክረዋል፡፡

ሐምሌ 2 ቀን 1995ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ደርባን ወደ አፍሪካ ሕብረት ሥያሜውን የቀየረው የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታው ግንቦት አጋማሽ ነበር፡፡ ቅኝ ግዛት ካስከተለው ምዝበራ በላይ ጥሎት ያለፈው የሥነ-ልቦና ስብራት እና ጠባሳ በቀላሉ የሚሽር አልነበረም፡፡

በዚያ አስከፊ የባርነትና የቅኝ ግዛት ዘመን ነጻነቷን በልጆቿ አጥንት እና ደም አስከብራ የዘለቀች ነጻዋ ኢትዮጵያ ባትገኝ ኖሮ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መመስረት ቀርቶ ማስብ እንኳን የሚቻል አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ለዘመናት የዘለቀው የቅኝ ግዛት ወረራ አፍሪካዊያንን ሀብታቸውን እና ጉልበታቸውን ብቻ ሳይኾን ሥነ-ልቦናቸውንም ሰልቦት ነበርና ነው፡፡ በወቅቱ ነጻ አህጉራዊ ድርጅት መመስረት የሚቻልበት አውድ ፈጽሞ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡

ሃጋይ አርሌክስ ስለ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ግለ ታሪክ በጻፈው መጽሐፉ “ድህረ-ቅኝ ግዛት ለአፍሪካ ሀገራት የባሰ ጨለማ ኾኖ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ እና ንጉሠ ነገሥቱ ባይኖሩ ኖሮ የአፍሪካ ሀገራት ማንሰራራት ባልቻሉም ነበር” ይላሉ፡፡ በወቅቱ ነጻነታቸውን ያገኙ አፍሪካዊ ሀገራት በሚከተሉት የድህረ ቅኝ ግዛት ፖሊሲ አንዱ ሀገር ሌላኛውን ሀገር በመንቀፍ ለሕብረት ቀርቶ ለጉርብትና እንኳን ተቸግረው ነበር፡፡ ይህ ደግሞ አህጉሪቷን በተሻለ ቁመና ላይ እንዳትገኝና እውናዊ ነጻነቷን እንዳታጣጥም አድርጓታል፡፡

ከቅኝ ግዛት ቀንበር ነጻ የወጡ ሀገራትን አስተባብሮ እና አሰባስቦ ነጻ አህጉር መመስረት ዘላቂ መፍትሄ መኾኑን ያጤነችው ኢትዮጵያ አድካሚውን እና ውስብስቡን ጉዞ ጀመረች፡፡ ምዕራባዊያኑ ህልም ያሉትን የሕብረት እና የአንድነት ጉዞ የጀመረችው ኢትዮጵያ የአንድነት ድርጅቱን ምስረታ የሚያከስሙ ፈተናዎች የገጠሟት ግን ከአህጉሪቷ ውጭ ሳይኾን ከአህጉሪቷ መካከል ነበር፡፡ ወቅቱ ከቅኝ ግዛት ቀንበር ነጻ የወጡ 32 የአፍሪካ ሀገራት ቢኖሩም በመጻዒዋ ነጻ አፍሪካን በመመስረት ሂደት በሁለት ዋና ዋና ጎራዎች ተከፈሉ፡፡

ካዛብላንካ እና ሞኖሮቪያ ለአንድ ዓላማ የተለያየ መንገድን መረጡ፡፡ የተለያዩትን ሰብስባ፣ የተበተኑትን ሸክፋ እና የተኮራረፉትን አቀራርባ ነጻ አህጉር የመመስረቱ ኅላፊነት የወደቀው ደግሞ በነጻዋ ሀገር ኢትዮጵያ ላይ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በወቅቱ በተደጋጋሚ የተቃጣባትን የቅኝ ግዛት ሙከራ በጀግንነት አክሽፋ ብቸኛዋ ቅኝ ያልተገዛች ነጻ ሀገር በመኾኗ ሁሉም ነጻ የወጡ ሀገራት ኢትዮጵያን መያዝ ይፈልጉ ነበርና በየአካባቢው በሚደረግ የነጻዋ አህጉር ምስረታ ምክክር ላይ እንድትገኝ ግብዣ ይደርሳታል፡፡

አፍሪካ በፖለቲካ እና በምጣኔ ሀብት ራሷን መቻል አለባት፡፡ ለዚህም ሀገራቱ በኮንፌዴሬሽን አንድ መኾን አለባቸው የሚል አቋም የሚያራምዱት የካዛብላንካው ቡድን በታዋቂዎቹ የነጻነት ታጋይ መሪዎች የጋናው ኩዋሚ ንክሩማህ እና በጊኒው ሲኩቱሬ እየተመራ ስድስት ሀገራትን አቅፏል፡፡ በሌላ ጎራ አፍሪካ ከገባችበት ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ለመውጣት የሌሎች ሀገራት እና አህጉራት ድጋፍ ያስፈልጋታል የሚል አቋም ያላቸው የሞኖሮቪያ ቡድን 22 ሀገራት ይገኛሉ፡፡

ኢትዮጵያ የምትፈልገው አህጉራዊ ሕብረት እና አንድነት ይመጣ ዘንድ እነዚህ ቡድኖች የያዟቸውን ልዩነቶች አጥብበው ወደ አንድ መምጣት ነበረባቸው፡፡ ኢትዮጵያ 1954 ዓ.ም ላይ ከሁለቱም ጎራዎች የተሳትፎ ጥሪ ቀረበላት ቀጣዩን አንድነት ለማምጣት ያስችል ዘንድ ናይጀሪያ ሌጎስ ላይ ተገኘች፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ የቀጣዩ ስብሰባ አዲስ አበባ እንዲኾን ግብዣ አቅርባ ተመለሰች፡፡

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የሁለቱን ጎራዎች ልዩነት አጥብባ ወደ አንድ ለማምጣት ሥራ ጀመረች፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ እና ማሳመን በኋላ በ1955 ዓ.ም ግንቦት ወር አጋማሽ ላይ 32 ነጻ የአፍሪካ ሀገራት የአንድነት ድርጅትን ለመመስረት አዲስ አበባ ላይ ለመገኘት ቀነ ቀጠሮ ያዙ፡፡ ከዲፕሎማሲያዊ ጥረት ጎን ለጎን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሰብሰቢያ አዳራሽ የገነባችው ኢትዮጵያ በተለየ ድምቀት መሪዎቹን ተቀብላ ስብሰባውን አስጀመረች፡፡ መሪዎቹ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስብሰባውን እንዲመሩ በሙሉ ድምጽ በመመረጣቸው ሰብሰባውን በታሪካዊ የመክፈቻ ንግግራቸው አስጀመሩ፡፡ “ታሪክ ሕያው ምስክር ነው፤ ይህ ቀን የአፍሪካዊ ቀን ተብሎ ይከበራል” ሲሉ ተደመጡ፡፡ በመጨረሻም የአፍሪካ መሪዎች የአንድነት መተዳደሪያ ቻርተርን ተፈራረሙ፡፡ ቻርተሩም በአማርኛ፣ በአረብኛ፣ በፈረንሳይኛ እና በእንግሊዝኛ ተዘጋጅቶ ታተመ፡፡ በዚህም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ እውን ኾነ፡፡

በምስረታው የተዘባበቱ ሁሉ ዐይን እና ጆሮዋቸውን አዲስ አበባ ላይ አሰነበቷቸው፡፡ አድካሚው የአንድነት እና የሕብረት ጉዞ በድል ተጠናቆ ምስረታው እውን ኾነ፡፡ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት ለአህጉሪቷ የሚጠበቅበትን ያህል ሰርቷል የሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚያሻው ቢኾንም ኢትዮጵያ ግን በአህጉራዊ ትብብር ዙሪያ የበረታች መኾኗን አረጋገጠች፡፡

የያኔው በኢትዮጵያ ማመን እና ኢትዮጵያን መከተል ዝም ብሎ የመጣ ተዓምር አይደለም፡፡ ከመሪው እስከ ተመሪው ለሀገሩ ቅድሚያ በመስጠቱ እና ሀገሩን የሌሎች መመኪያ በማድረጉ ተናግራ የምትሰማ ሀገር ለመፍጠር እንደተቻለ በርካቶች ይስማማሉ፡፡ ኢትዮጵያ ምን ያክል አህጉራዊ መሪነቷን አስቀጥላለች? የሚለው ግን ምላሽ የሚያስፈልገው ጥያቄ ነው፡፡

ምንጭ፡- ሃጋይ ኤርሊክ “ኃይለ ሥላሴ ግለታሪክ” እና ኤርሚያስ ጉልላት “ቀ ኃ ሥ እና ፓን አፍሪካኒዝም” መጽሐፍት ናቸው፡፡

በታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!