ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 23ኛ መደበኛ ስብሰባው፤ ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረት እና በታክስ ላይ የሚፈጸመውን ማጭበርበር ለመከላከል የቀረበውን አዋጅ አጽድቋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ ሪፖርት እና የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክረሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እና በግራንድ ዱቺ ኦፍ ሉዘምበርግ መንግሥት መካከል በገቢ ላይ የሚከፈለውን ግብር በሚመለከት ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረት እና በታክስ ላይ የሚፈጸምን ማጭበርበር ለመከላከል የቀረበው ስምምነት የሁለትዮሽ ትብብርን ለማጠናከር የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍን የሚፈጥር ረቂቅ አዋጅ እንደሆነ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ ገልጸዋል።
የውጭ የግል ካፒታል ፍሰት እና ኢንቨስትመንት በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ወሳኝ ድርሻ እንዳለው፣ በሁለቱ ሀገራት ለሚደረገው የንግድ ልውውጥ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንቅፋት እንዳይሆን እንዲሁም ስምምነቱ የሁለቱ ሀገራት ዜጎችን ብቻ ሳይሆን በሁለቱ ሀገሮች ነዋሪ የሆኑትንም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚስችል አዋጅ መሆኑን የተከበሩ አቶ ደሳለኝ ለምክር ቤቱ አብራርተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ከገንዘብ ሚኒስቴር የሕግ አማካሪ በተለያዩ መድረኮች በረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነት ላይ በሰፊው እንደተወያዩም አክለው ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም ረቂቅ አዋጁ በታክስ ማጭበርበር የሚታዩ ግድፈቶችን ለማረም የሚያስችል እና የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የሚያጠናክር አዋጅ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ምክር ቤቱ በውሎው ረቂቅ አዋጁን አዋጅ ቁጥር 1295/2015 አድርጎ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!