ተቋማት የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ ተባብረው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው የአማራ ክልል ሥራና ስልጠና ቢሮ አሳሰበ።

6
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ
ደብረ ታቦር:መጋቢት 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ጎንደር ዞን ሥራና ስልጠና መምሪያ ከወረዳ ተቋማት፣ ከአጋር አካላት፣ ከዞንና ወረዳ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ከሥራ ዕድል ፈጠራና ተያያዥ አሠራሮች ጋር በተያያዘ ምክክር እያደረገ ነው።
በመድረኩ አዲሱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ምክር ቤት ደንብ ይተዋወቃል ተብሏል። የመንግሥትና የግል ኮሌጆች ተማሪዎች በግሉ ዘርፍ ስልጠና ስለሚያገኙበት አሠራርና የግልም ሆነ የመንግሥት ተቋማት እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ለሥራ ዕድል ፈጠራው ጠንካራ እገዛ ስለሚያደርጉበት ሁኔታ እንደሚመክሩም ይጠበቃል።
የዞኑ ሥራና ስልጠና የ8 ወራት የሥራ አፈጻጸም ውይይት ተደርጎበት የቀሪ ጊዜያት የትኩረት አቅጣጫ ይመላከትበታል ነው የተባለው።
በምክክሩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ሥራና ስልጠና ቢሮ ኀላፊ አረጋ ከበደ የአማራ ክልል ከፍተኛ የገጠር ሥራ አጥነትና በየጊዜው የሚጨምር የተማረ ሥራ አጥ ቁጥር መኖሩን ጠቅሰው ተቋማት የሥራ አጡን ቁጥር ለመቀነስ ተባብረው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
በመድረኩ የአማራ ክልል ሥራና ስልጠና ቢሮ ኀላፊ አረጋ ከበደ እና የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ የደቡብ ጎንደር ዞን አመራር፣ በዞኑ ውስጥ የሚገኙ የግልና የመንግሥት ኮሌጆች፣ የወረዳ ኮር አመራሮች፣ አሥተባባሪዎችና የግል ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፦ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!