“ተማሪዎችን በየደረጃው በብሔራዊ ደረጃ መመዘን ሀገራዊ ዝግጅቱን ለመገምገም ያግዛል” ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ።

84
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ

ባሕር ዳር : ታኅሣሥ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር የምትሰራው በተማረ የሰው ሃብት፤ የምትፈርሰው ደግሞ በአግባቡ ባልተቀረጸ ጭንቅላት ነው፡፡ “የተማረ ይግደለኝ” የሚለው የሀገሬው ሰው ብሂል የሚያሳየውም ይኽንኑ ይመስላል፡፡ ያደጉ ሀገራት የእድገታቸው ምስጢር ሲፈተሸ ለትምህርት ያፈሰሱት መዋዕለ ንዋይ የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ ትምህርት እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ማሕበረሰብ ለመሰልጠን እርሾ ሆኖ ያግዛልና፡፡

“ሮም በአንድ ሌሊት አልተገነባችም” እንዲሉ የትምህርት የመጨረሻ ግብ በተወሰነ ጊዜ የማይለካ እና በተወሰነ መስፈርት ብቻ የማይመዘን የረጅም ጊዜ ሂደት ነው፡፡ የትምህርት የመጨረሻ ግብ ሂደታዊ መሆኑ ደግሞ በየደረጃው ክትትል እና ድጋፍ የሚያስፈልገው ዘርፍ አድርጎታል፡፡ የተማሪዎች ምዘና ከጀምላ ፍረጃ ወጥቶ ግለሰባዊ እውቀትን፣ ክህሎትን እና አመለካከትን ሊለካ የሚችል መሆን አለበት ያሉን ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ ናቸው፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዚዳንት፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ የሆኑት ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ እንደሚሉት የተማሪዎች የምዘና ሥርዓት የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያው አንድ የትኩረት አካል ነው፡፡ በየደረጃው የሚኖረው የምዘና ሥርዓት እውቀትን፣ ክህሎትን እና አመለካከትን በአግባቡ የሚለካ መሆን አለበት ይላሉ፡፡

ትግበራ ላይ በሚገኘው ሥርዓተ ትምህርት ላይ ተማሪዎች ስድስተኛ፣ ስምንተኛ እና 12ኛ ክፍሎች ላይ በብሔራዊ ደረጃ ምዘና እንደሚካሄድ ያሳያል ያሉት ፕሮፌሰር መንገሻ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለመግባት እና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም አጠናቆ ለመውጣት የመውጫ እና የመግቢያ ፈተናዎች ይዘጋጃሉ ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት እና ሰፊ የቆዳ ስፋት ያላት ሀገር ናት ያሉት ፕሮፌሰር መንገሻ በሁሉም አካባቢዎች ተመሳሳይ የትምህርት እድል አይኖርም ነው ያሉት፡፡ “ተማሪዎችን በየደረጃው በብሔራዊ ደረጃ መመዘን ሀገራዊ ዝግጅቱን ለመገምገም ያግዛል፤” እንደ ሀገር ያለንን ዝግጅት ለማወቅም ይረዳል ብለዋል፡፡

በደርግ ዘመነ መንግስት እና ቀድሞ በነበሩት የኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርቶች ላይ ተማሪዎች “ተርም” እየተባለ በአንድ ዓመት ሁለት ክፍሎችን ይዛወሩ ነበር ያሉት ፕሮፌሰሩ በትምህርት አቀባበላቸው የደከሙ ተማሪዎችም ክፍል የሚደግሙበት አግባብ ከፍተኛ የቁጥጥር ስርዓት የነበረው ነው ይላሉ፡፡ ተማሪዎችን በጀምላ መጣልም ሆነ በጀምላ ማሳለፍ የምዘና ሥርዓቱ ድክመት በመሆኑ የሥርዓተ ትምህርት መሻሻያው ለተማሪዎች ምዘና ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!