ብዙ ቋንቋ ይወራበታል፤ ሳይግባባ የተመለሰ ግን የለም። እኔም ለሥራ ወደ ስፍራው ስቀርብ ለሥራ የያዝኳቸውን ዕቃዎች እንድሸጥ ተጠይቄ ነበር።

1
152

ባሕር ዳር፡ መስከረም 29/2012 ዓ/ም (አብመድ) ኢትዮጵያውያን ዘመን ሳይዘምን የዘመኑ፣ ዘመንን የዋጁ፣ ለዓለም ብርሃን የፈነጠቁ ድንቅ ሕዝቦች ናቸው። የዓለም ሕዝብ ኑሮው በዱር በገደል በነበረበት በዚያ ዘመን ኢትዮጵያውያን ቀለም በጥብጠው፣ ብራና ፍቀው፣ ፊደል ቀርፀው፣ ሰዋሰው ሰድረው፣ ዓረፍተ ነገር አሰካክተው ታሪክ ይጽፉ ነበር። ኢትዮጵያውያን በብዙ ቋንቋ የተናገሩ፣ በኅብረ ብሔራዊነት ያማሩ፣ በአንድ ልብ የመከሩ በአንድ ቃል የመሰከሩ ድንቆች ነበሩ። ከደቡብ እስከ ሰሜን፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከጫፍ እስከጫፍ ከአፍ እስከ ገደፍ ድረስ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ጉዳይ አንድ ሐሳብ አንድ ምክር ብቻ ነበራቸው።

“መንገድ ዘወርዋራው ይወስዳል፤ ያመጣል” እንዲሉ እማ የአምባሰል፣ የአንቺ ሆዬ፣ የትዝታና የባቲ ቅኝቶች እናት፣ የንጉሥ ሚካኤል ርስት፣ የፍቅር ተምሣሌት፣ የመቻቻል ምልክት ወደ ሆነችው የወሎ ምድር ድንገት አቀናሁ። የወሎን ምድር ሲረግጡ ጥርሳቸው ፈልቀቅ ሲል ልብን የሚያጠፉ ቆነጃጅትና ጎፈሬያቸውን ነቅሰው የሚንጎማለሉ ኮበሌዎች ማየት የተለመደ ነው። ቆንጆ የሚወልደው ምድሩ ወይስ ውኃው ወይስ ሰዎቹ ብለው መገረምዎ አይቀርም።

ባቲ በደቡብ ደዌ ሀረዋ፣ በሰሜን ወረባቦ፣ በምዕራብ ቃሉ፣ በምሥራቅ በአፋር ክልል ትወሰናለች። የራሷን ቅኝት ተቀኝታለች፤ስሟ በሀገሩ ናኝቷል። ያላዩትን በምኞት ያዩትን ደግሞ በናፍቆት አሳምማለች።

“ ኧረ ባቲ ባቲ፣

ባቲ ገንደላዩ ፣

ሃድራው የሚሞቀው ደራርበው ሲተኙ” የምትለዋን ስንኝ ብቻ ላስታውሳችሁ። ባቲ አዲስ አበባ ሳትቆረቆር፣ የመርካቶ ገበያ ሳይታለም፣ ከአሰብ፣ ከቀይ ባሕር፣ ከወሎ፣ ከሸዋ፣ ከአፋር፣ ከትግራይ፣ ከጅቡቲ የመጡን ሁሉ  የምታገናኝ ታላቅ መዳረሻ ነበረች። ምን አልባትም በሰሜን ምሥራቅ የኢትዮጵያ ክፍል ታላቁ ገበያ እየተባለ የሚጠራው የባቲ ገበያ ነበር፤ ነውም። ይህ ገበያ ሰኞ ቀን የሚውል ስለሆነ “ሰኞ ገበያ”  ይባላል። በገበያው የሚችሉትን ሁሉ ቋንቋ ይናገራሉ፤ የፈለጉትን ሁሉ ይሸምታሉ፤ ይሸጣሉ።

“ ምነዋ ግመሉ ጉልበቱ ፈሰሰ፣

ቀይ ባሕር ተጭኖ ባቲ እየደረሰ።” ተብሎ የተገጠመላት ይቺ ታሪካዊት ምድር አማራ፣ አፋር፣ አርጎባ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ሶማሌ እና ሌሎችም የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአንድ ገበያ ስር የሚገናኙባት ባቲ ነች። በባቲ ገበያ ዘር፣ ብሔር፣ ጥላቻና ሽኩቻ እንዳይደርሱ ርቀው፣ እንዳይቀርቡ ተሸማቅቀው ከጠፉ ዘመናት አልፈዋል።

ከደራው ገበያ ቅኝቴ መሀል በረድፍ ተቀምጠው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የሚጨዋወቱ አባቶችን አገኘሁ፤ ሠላምታ ተለዋወጥን፡፡ ስለገበያውም ጠየኳቸው። መጀመሪያ መልስ የሰጡኝ አባት አብዱ ሁሴን ይባላሉ። ባቲ ዙሪያ ተወልደው ያደጉ ናቸው። “ልጄ እዚህ ገበያ የማይመጣ የለም፤ የማይሸጥም የለም። ብዙ ቋንቋ ይወራበታል፤ ሳይግባባ የተመለሰ ግን የለም።” አሉኝ።

ነገሩን የበለጠ ግልፅ እንዲያደርጉልኝ ጠየኳቸው “ለገበያ የመጣው ሁሉ በሚችለው ቋንቋ ያወጋል። አምስት ቋንቋ የሚችል ሰው አለ፤ ገዡ የሻጩን ቋንቋ ባይችል እንኳን አብሮት ከተቀመጠው ቋንቋውን የሚችል ስለማይጠፋ ቋንቋ ይበደራል፤ ከዛም ይገበያያሉ” አሉ ፈገግ እያሉ።  ልብ ይበሉ ደጉ ትውልድ  ቋንቋ ተበዳድሮ አብሮ ይኖራል። ክፉው ትውልድ  ደግሞ ዘር ቆጥሮ ይራራቃል ።

ሌላኛው ሰው የሱፍ ብሩ ይባላሉ። በባቲ ተወልደው በዚያው አድገዋል። አማርኛ፣ አፋርኛና ኦሮምኛ አቀላጥፈው ይናገራሉ። “ልጄ ባልከፋው ዘመን ማር፣ ቅቤ፣ እህል፣ ስጋ ሌላውም የሚበላውና የሚጠጣው ርካሽ  ነበር።  ብር ግን ውድ ነበር። አንድ ሺህ ብር ሞልቶ የሚይዝ ሰው አይገኝም ነበር። አሁን ያ ደግ ዘመን አልፎ ገንዘብ ረከሰ አቅም አጣ የቀደሞቹ ደግሞ ተወደዱ፡፡”  የሱፍ ብሩ ቀጠሉ ከቀይ ባሕር፣ አሰብ፣ ትግራይ፣ ከአባይ መለስ ወሎና ሸዋ፣ አፋር፣ ሶማሌ ጅቡቲ ድረስ ሰዎች ተሰባስበው በዚያች ገበያ ስር እንደሚገበያዩ ነገሩኝ። “ፍቅራችን ልክ የለውም፤ ቀኑ ደርሶ እስከምንገናኝ እንነፋፈቃለን። ምን አደከመህ ልጄ ገበያው የሸቀጥ መለዋወጫ ብቻ አይመሰልህ የፍቅርም መወጫ ነው።”

ከነዚያ የኤርትራ ነጋዴዎች ወርቅ፣ ብርና ሌሎች ጌጣጌጦች፣ ከአፋር ነጋዴዎች ግመል፣ ቅቤና ፍየል፣ ከሌላውም አካባቢው የሚያፈራውን እየያዙ ሳምንት በገባ ሰኞ የማይቀርበት ታላቅ ቀጠሮ ባቲ ላይ እንደነበር አቶ የሱፍ ነግረውኛል። ከአሰብ የሚመጡ ነጋዴዎች ግመላቸውን ጭነው ለመምጫ 14 ቀን ለመመለሻም 14 ቀን ይጨርሱ እንደነበርም ያስታውሳሉ።

“ቆይቶማ ዓለሙ ጊዜ መጣ ተብሎ፣ የእግር ጉዞ ቀርቶ፣ መኪና መንገድ ሲሰራ አሰብም ተዘጋ ፍቅርም እየራቀ ሄደ። አሁንም ተከፍቶ ደስታችን ሳያልቅ እያስፈራሩን ነው” አሉ አቶ የሱፍ የቀደመውን አሰብና አሁን ላይ በአሰብ ላይ ያላቸውን ስጋት በሚገልፅ መልኩ። መች ይህ ብቻ! አሁን ላይ ባቲ ሰኞ ገበያ የሚቃጠሩት ኢትዮጵያውያን በቀጠሯቸው አለመገናኘት አሳስቧቸዋል።

ያ የቀደመ ፍቅር በታመመው ፖለቲካ ሊነካ ዳር ዳር እያለ እንደሆነም ሰምቻለሁ። ቀደም የነበረው ትውልድ የባቲ ሰኞ ገበያን መድረሻ ቀን ቆጥሮ ይገናኝ ነበር። የአሁኑ ደግሞ ዘር መቁጠር ሲያመጣ ጥርጣሬ እየፈጠረ እንደሆነም ነግረውኛል። ግን አባቶቹ ‹‹ረጅም ዘመን በፍቅር ያሻገረን አምላክ በአጭር ዘመን ጥላቻ እንደማይለያዬን እናምናለን›› ብለውኛል። የአሁኑ ፖለቲካ መንሻፈፍ ለእነርሱ ስጋት ይሁን እንጂ ከአሰብ የሚመጡት ቢቀሩም ሌሎች ኢትዮጵያውያን ከአንድ ገበያ ስር የኢትዮጵያዊነትን ትስስር እያሳዩ አሁንም አሉ። ትላንትም ነበሩ። ነገም እንደሚኖሩ የጠነከረ እምነት አለኝ።

ታሪክና ምክር ከአባቶች ተቀብዬ አመሥግኜ ተነሳሁ።  ገበያውንም ድጋሜ መቃኘት ጀመርኩ። የገበያ ዕቃ ይዘው የሚመጡ ግመሎች  በአንድ ረድፍ፣  የሚሸጡት በሌላ ረድፍ፣ ማሩ፣ የቅቤው፣ ቅመማቅመሙ፣ አልባሳቱ፣ ጌጣጌጡ እና የሌላውም በየዓይነቱ ተሰልፎ ተመለከትኩ።

ከሁሉም ግን ቀልቤን የሳበው የቁም ገበያ የሚባለው ነበር። የቁም ገበያ ላይ መቀመጥ አይቻልም። አጥብቆ መከራከርም እንደዚሁ። በተለይ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች የሚሸጡት የቁም ገበያ ላይ ነው። ገበያው እጅግ ፈጣን የሆነ የእጅ በእጅ ገበያ ነው። ወደ ቦታው የተጠጋ ሁሉ ወይ ይጠየቃል ወይ ይጠይቃል። እኔም ለሥራ ወደ ስፍራው ስቀርብ ለሥራ የያዝኳቸውን ዕቃዎች እንድሸጥ ተጠይቄ ነበር።

ከኢትዮጵያውያን ጋር በየሳምንቱ ባቲ ሰኞ ገበያ ላይ ለመገናኘት ቀጠሮ እንዳልይዝ አልችልም፤ እንዳልቀር ደግሞ አይረሳኝም። ከደራው ገበያ መካከል ቆሜ የኢትዮጵያውያንን አብሮነት እያደነቅሁ ፈዝዣለሁ። ለመራቅም ጨነቀኝ፤ የሆነው ሆነና መውጣት አይቀርም፤ ለመውጣት ተገደድኩ።

ወዳጄ ስለኢትዮጵያውያን መስተጋብር የተፃፈ መጽሐፍ ብታነብ “ውሸት ይሆን?” የሚል ጥርጣሬ ያድርብሃል። ሰው ነህ እና ግድ የለም ተጠራጠር፤ ወይም የመጽሐፉ ብራና ይበዛብህና ደክሞህ ትተወዋለህ፤ ይኼም የሰው ባሕሪ ነውና ቅቡል ነህ።  ወይም ጊዜ አግኝተህ  ብታነበው  አልታደል ብለህ ስለኢትዮጵያ፣ ስለኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊነት ያነበብከው መጽሐፍ የውሸት ይሆን እና በሌለ ታሪክ ላይ ስትባዝን ትኖራለህ። ኢትዮጵያን፣ ኢትዮጵያውያንንና ኢትዮጵያዊነትን ለማዬት ከፈለክ ወደ ባቲ ሰኞ ገበያ ሂድ። አትጠራጠር ባይንህ ታያለህ፣ አይተህም በፍቅር ትማረካለህ፤ በአንድነት ትበረታለህ። ያን ጊዜ ኢትዮጵያውያን ምን ዓይነት ድንቅ እና ብርቅ የሆኑ ዜጎች መሆናቸውን ትገነዘባለህ።

የመከራው ነፋስ ይመለስ፤  የሠላሙ ነፋስ ይገስግስ፤ ኢትዮጵያውያን ይንገሡ፤ ክፉዎችም ይፍረሱ። ሠላም!

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here