ብዙዎች የሞቱለትን ዓላማ ለማሳካት ወቅቱ የሚጠይቀውን ተጋድሎ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የባሕር ዳር ከተማ ወጣቶች ተናገሩ፡፡

0
107

ብዙዎች የሞቱለትን ዓላማ ለማሳካት ወቅቱ የሚጠይቀውን ተጋድሎ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የባሕር ዳር ከተማ ወጣቶች ተናገሩ፡፡

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 01/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ሰማዕታት የሞቱለት ዓላማ እንዲሳካ የአሸባሪውን ትህነግ ርዝራዦች ከምድረገጽ ማጥፋት ይገባል ሲሉ ነሐሴ 1/2008 ዓ.ም ከትህነግ ተላላኪዎች በተከፈተባቸው ተኩስ የተጎዱ ወጣቶች ተናገሩ፡፡ ነሐሴ 1/2008 ዓ.ም የተደረገው ሕዝባዊ እምቢተኝነትና የነጻነት ተጋድሎ አምስተኛ ዓመት ዝክረ ሰማዕታት ዛሬ በባሕር ዳር ተካሂዷል፡፡

በወቅቱ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል አሚኮ ያነጋገራቸው ወጣቶች እንዳሉት ብዙዎች የሞቱለትን ዓላማ ለማሳካት ወቅቱ የሚጠይቀውን ተጋድሎ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

አሸባሪው ትህነግ መራሽ ሥርዓት ለዓመታት በሕዝብ ላይ ተነግሮ ማለቂያ የሌለው በደል አድርሷል፡፡ ነሐሴ 1/2008 ይህንን ችግር ለማስወገድ የባሕር ዳር ከተማ ወጣት በነቂስ ወጥቶ የአሸባሪውን ትህነግ ቡድን ዙፋን የነቀነቀበት ዕለት ነው፡፡ በዕለቱ የቡድኑ ተላላኪዎች ባዶ እጃቸውን አደባባይ ወጥተው በተቃወሙ ወጣቶች ላይ ቃታ ስበው የተኩስ ሩምታ ከፈቱ፤ ከድምጽ አልባ እስከ ተተኳሽ መሳሪያ በመጠቀም መግደል፣ ማቁሰልና ማሠር ጀመሩ፡፡

ወጣት ሻምበል ኀይሉ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ነው፡፡ ለዓመታት በአማራ ሕዝብ ብሎም በኢትዮጵያውያን ላይ ሲደርስ የነበረውን በደል በመቃወም አደባባይ በመውጣቱ በጥይት ተመትቶ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ የተቃውሞ መፈክር ይዞ ከፊት ይመራ ነበርና አልሞ ተኳሽ ባነር የያዘበትን ቀኝ እጁን በጥይት መታው፡፡ ወጣት ሻምበል በዕለቱ ብዙዎች መሞታቸውን፤ ብዙ አረጋውያን ያለጧሪ፣ ሕጻናት ያለ አሳዳጊ መቅረታቸውን፣ ብዙዎች ደግሞ ለቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መዳረጋቸውን አስታውሷል፤ በዚህም ቀላል የማይባል ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንደደረሰባቸውም ተናግሯል፡፡ ምንም እንኳን ክስተቱ አሳዛኝ ቢኾንም ከተሰለፉለት ዓላማ አንጻር ነሐሴ 1/2008 ዓ.ም ሀገራዊ እምቢተኝነቱን ያጠናከረ ዕለት መኾኑን አስታውሷል፡፡

በስላም ቀንዲሎቹ መታሰቢያ ላይ የተገኙ ወጣቶች እንዳሉት ወጣቱ በቅጡ ሳይደራጅና መሣሪያ ሳይታጠቅ የአሸባሪውን ትህነግ መንበር ነቅንቋል፡፡

ከቤተመንግሥት ወደ መቀሌ፣ ከመቀሌ ወደ ቆላ ተንቤን የቀበሮ ጉድጓድ፤ ከመንግሥትነት ወደ ተራ አሸባሪነት እንዲለወጥ በማድረግ ትልቅ ፖለቲካዊ ድል ተቀዳጅቷል፡፡

ሌሎች ወጣቶችም ወጣቱ ባዶ እጁን ወጥቶ አሸባሪውን ትህነግ ከመንግሥትነት ወደ ተራ ሽፍትነት እንደቀየረ መገንዘብ አለባቸው ነው ያሉት፡፡ የአማራ ሕዝብና ኢትዮጵያውያን ነጻ እስኪወጡ ትግሉ መጠናከር እንዳለበትም አንስተዋል፡፡

የአሸባሪውን ቡድን ርዝራዦች አጥፍቶ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት መሰለፍ አለበት ብለዋል፡፡ መሪዎች ሕዝቡን በመምራት፣ ወጣቱም ግንባር ድረስ በመሰለፍ፣ የሃይማኖት አባቶች ጸሎት በማድረግ፣ አቅም የሌላቸው ደግሞ ስንቅና ትጥቅ በማቀበል መረባረብ ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡ ሁሉም በአቅሙ ከታገለ አሸባሪው ትህነግን በአጭር ጊዜ ማጥፋት እንደሚቻል ወጣቶቹ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡-ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m