ጎንደር: ታኅሣሥ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ያማረው ነገር ይበቅልበታል፣ የተወባው ነገር ይታይበታል፣ አራሽና ተኳሽ፣ ጎበዝና ገበዝ፣ ደፋርና ኩሩ ይወለድበታል። በኩራት ያድጉበታል፣ በጀግንነት ይኖሩበታል፣ በግርማ ይመላለሱበታል። የሚዘራው ይበቅላል፣ የበቀለው ያብባል፣ ያበበው ያፈራል፣ የተባረከ ምድር፣ የተወደደ አድባር ነው።
የነገሥታቱን ከተማ በራስጌው፣ አምሳለ ልብ፣ አብረቅራቂ ወርቅ የኾነውን ሐይቅ በግርጌው አድርጎ በውበት ይኖራል፣ አረንጓዴ ካባ ለብሶ በሞገስ ይከርማል። ውብ ምድር ነው ሲያዩት ደስታን ይሰጣል፣ ልብን በሃሴት ይይዛል። እንደ መዳፍ በለሰለሰው ምድር፣ ጣና በሞሸረው፣ ውበትና ግርማ በኾነው አድባር እንደ ንብ የሚታትሩ ብርቱ ገበሬዎች፣ እንደ አንበሳ የሚያገሱ ጀግኖች፣ እንደ ነብር ጥቃት የማይወዱ ልበ ሙሉዎች፣ ሀገር ወዳዶች፣ ሠንደቅ አክባሪዎች ይኖሩበታል።
ከመናገሻዋ ከተማ፣ ከፋሲል ደጅ፣ ከታላላቆቹ ሠገነት ላይ ቆሜ ከጣና ሐይቅ ዳር ያለውን ምድር ተመልክቻለሁ፣ በአየሁትም ነገር ሀሴትን አድርጌያለሁ፣ እንደ መዳፍ ለስልሶ፣ አረንጓዴ ካባ ለብሶ የሚታየው ምድር በአሻገር ይጣራል፣ ኑ ኑ ይላል። ከሰገነቱ ወርጄ፣ በፋሲል ደጅ ተረማምጄ፣ ድማዛን አልፌ ወለል ወደአለው ሜዳ ወርጃለሁ። ምድሩ ያምራል፣ ቀዬው ልብን ይሠርቃል፣ ግርማ ሞገስ ያላቸው ደጋጎች ያሉበት፣ በግርማና በኩራት የሚኖሩበት ነውና ደስታን ይሰጣል። ባለቅኔዎች የተቀኙበት፣ ዓለም አጫዋቾች ያዜሙለት መልካሙ ምድር ነው ደምቢያ።
ደምቢያ ሲነሳ ኩራት፣ ጀግንነት፣ ታማኝነት፣ ልበ ሙሉነት፣ ሀገር ወዳድነት፣ ለሠንደቅና ለሀገር ራስን አሳልፎ መስጠት፣ ጠንክሮ መሥራት አብረው ይነሳሉ። አሳው፣ ጤፍና ሽንብራው፣ ጠጅና ማሩ፣ ወተትና ቅቤው አብረው ይታወሳሉ። የደምቢያ ጀግኖች፣ የደምቢያ ደጋጎች፣ የደምቢያ ልበ ሙሉዎች በርትተው ይሠራሉ፣ ከላሞቻቸው ወተት ያልባሉ፣ በበሬዎቻቸው እሸት ይበላሉ፣ ሲሻቸው በምንሽር፣ ሲሻቸው በክላሽ፣ ሲሻቸው በቤልጅግ ዓልመው ይተኩሳሉ፣ ጠላት በተነሳ ጊዜ አንድ ጥይት ለአንድ ጠላት ያድላሉ። ስሞት አፈር ስኾን እያሉ የተራበውን ያጎርሳሉ፣ የተጠማውን ያጠጣሉ።
በቀዬው ወተትና ማር አይታጣም። የወተቱ ምንጭ የማሩ ሥፍራ አይነጥፍም። መልካም ምድር። ከተዋበው ምድር ደምቢያ ደርሻለሁ። አረንጌዴ ካባ ከለበሰው ቀዬ ውስጥ ገብቻለሁ። ከደጋጎቹ ጋር ተቀላቅያለሁ። ደምቢያ ደርሶ ታታሪ አርሶ አደሮችን ሳይጠይቁ መምጣት መልካም አይደለምና ወደ አንድ ግርማ ያለው መንደር ለመሄድ ተነስቻለሁ። ጀንበር በማለዳ መሞቅ ጀምራለች። ለሥራ የሚታትሩ የቀዬው ሰዎች እየተፋጠኑ ነው። እረኞች ከብቶቻቸውን ነድተው ወጥተዋል፣ ሁሉም በየፊናው በሥራ ተጠምዷል።
መልካሙን ምድር እየቃኘሁ መዳረሻዬ ወደኾነችው መንደር ገሰገስኩ። ቀዬው ረጃጅም ዛፎች የበዙበት፣ አትክልቶች ያስጌጡት፣ የደከመው የሚያርፈበት፣ የጠማው የሚጠጣበት ውብ ስፍራ ነው። በዚያ ቀዬ ውስጥ መልካምነት የበዛ ነው። በማለዳ ሙቃ የነበረችው ጀንበር በአረንጓዴ ዛፎች ምክንያት ጉልበት ያጣች ትመስላለች። በአረንጓዴ ዛፎች በተከበበው መንደር ውስጥ ባለች ቀጭን መንገድ ውስጥ ለውስጥ ገሰገስኩ። ወደ ውስጥ በዘለቁ ቁጥር የበለጠ እየተዋበ ይሄዳል። ውበቱን እያደነቅኩ ወደውስጥ ዘለኩ።
ወደ ውስጥ የበለጠ ስጠጋ በዚያ በአማረና በተዋበ ለምላሜ ሥፍራ ታላቅ ቤት ተመለከትኩ። ባየሁት ነገር አብዝቼ ተገረምኩ። የቤቱ ዙሪያ ገባ በአረንጓዴ የተከበበ ነውና የአንድ ገጠር ውስጥ ያለ መኖሪያ ሳይኾን ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ያለው ቤተመንግሥት አስመስሎታል። በረጃጅም ዛፎች ላይ ኾነው በሕብረ ዝማሬ ከሚዘምሩ አዕዋፋት በስተቀር የሚሰማ ድምፅ የለም። ዝም ባለው ውብ ሥፍራ የሚሰሙት አዕዋፋት ለውቡ ሥፍራ ተጨማሪ ውበት ሰጥተውታል። ሥፍራው ብርቱ እጆች ያሳመሩት፣ ደጋጎች የሚከቡት ነው። ፃዲቃን የሚሰባሰቡበት፣ በፀጥታና በድርጋታ የሚኖሩበት ይመስላል።
እነኾ ይህ ቤት በሀገር ላይ የነገሡ ነገሥታት የሚመላለሱበት፣ የጦር አለቆች እና የእልፍኝ አስከልካዮች በዙሪያ ገባው የሚቆሙበት ቤተመንግሥት ሳይኾን ከበሬዎቹ ጋር በማሳው ላይ የነገሠ አርሶ አደር ቤት ነው። በዚያ ባማረ ግቢ ውስጥ የተቀመጡ አንድ ባለ ግርማ ሞገስ ሰው ተመለከትኩ። ወደ ውስጥ ዘልቄ ሰላምታ ሰጠዃቸው። ከመቀመጫቸው ተነስተው፣ ልብን በሚሰርቅ ለዛቸው አፃፋውን መለሱልኝ። ወደ ውስጥም እየገባ ዘንድ ጋበዙኝ። ወርቄ ካሳውደግ ይባላሉ። ደምቢያ ውስጥ መቋሚያ በተባለች ሥፍራ ነው የሚኖሩት። ንብ በማነብ፣ አትክልት በመትከል እና ሌሎች የግብርና ሥራዎችን በመሥራት ይተዳደራሉ። ከሌሎች ቤቶች ፈንጠር ብሎ የተሠራው ቤታቸውን በአትክልትና ፍራፍሬ አስጊጠውታል። ዙሪያ ገባውን በንብ ቀፎ አሳምረውታል።
ግቢያቸውን እያሳዩኝ ብዙ ነገሩኝ። ” ቀደም ሲል ኑሮዬ ከእጅ ወዳፍ ነበር። አሁን ግን ንብ እያነብኩ አትክልት እየተከልኩ የተሻለ ሕይወት መኖር ጀምሬያለሁ።” ነው ያሉኝ። እሳቸው በተለያዩ አካባቢዎች ለሥራ ሲመላለሱ ያዩትን መልካም ነገር በግቢያቸው መተግበራቸውንም ነግረውኛል። ” ልጄ አሁን ሁሉንም ተወው ግቢውን እየዞርኩ ሳዬው የማየው ነገር ብቻ ያጠግበኛል።” ነው ያሉኝ።
እኒያ በብርታት ንብ እያነቡ ማር የሚያመርቱት ጥንካራ ሰው የማር ምርቱ አዋጭ መኾኑንም ተናግረዋል። የቤታቸው ዙሪያ በባሕላዊ፣ የሽግግር እና ዘመናዊ በሚሏቸው የንብ ቀፎዎች የተዋበ ነው። በዚያ ባመረ ግቢ ውስጥ ከንብ ድምፅና ከአዕዋፋት ዝማሬ ውጭ ዝምታውን የሚያናጋ ድምፅ አይሰማም። ” መሬት መቦዘን የለበትም፣ ግቢዬ አረንጓዴ እንደኾነ ለዓመት ይዘልቃል፣ አትክልቱ ለዓይኔ ማረፊያ ይኾናል፣ ለንቦች ቀሰምም ይኾናል፣ ማዕዛው ደግሞ የበለጠ ያስደስተኛል፣ የግቢው አትክልት ለንብ የተመቼ ነው፣ ብትፈልግ ታርፈበታለህ፣ ብትፈለግ ቆርጠህ ትመገበዋለህ፣ እንዴው ሌላው ይቅር ንቦቹ እንደልባቸው ቀሰም ያገኙበታል” ነው ያሉኝ።
እኒያ በቤታቸው ዙሪያ እንዳሰለፏቸው የንብ መንጋዎች ሁሉ ያለ ሥራ ውለው የማያድሩት ብርቱ ሰው የንብ መንጋዎቻቸውን የሚፈትንባቸው ጉዳይ እንዳለም ነግረውኛል። ለዓረም ተብሎ የሚረጭ ኬሚካል ንቦቻቸውን እንደሚገድልባቸው ነው የተናገሩት። አንዳንድ ሰዎች ፀረ አረሙን ሌሊት እንዲረጩ እየጠየቁና ዘመናዊ ቀፎዎቻቸውን እየዘጉ ንቦቻቸውን እንደሚያተርፉም ነግረውኛል። ያም ኾኖ ችግሩን እየተቋቋሙ በተዋበው ግቢ ውስጥ የማረውን ማር ያመርታሉ፣ ልጆቻቸውን እና የልጅ ልጆቻቸውን በደስታ ያኖራሉ፣ አሁን ቀን ቢጎድል የሚሞሉበት፣ ቢቸግራቸው ችግራቸውን የሚወጡበት ተቀማጭ ገንዘብ በባንክ እንዳላችም ነግረውኛል። እኒያን ብርቱ ሰው ከተማ የመግባት ሀሳብ እንዳለቸው ጠይኳቸው” አይ ልጄ ከተማ ምን ያደርግልኛል፣ ይሄን የመሠለ ሥፍራ ጥዬ ለምን እሄዳለሁ፣ ከሠራህ እና ካሰመርከው ገጠሩም ከተማ ነው። ባለሁበት የተመቻቸ ሕይወት እኖራለሁ፣ ከተማ የመግባት እቅድ የለኝም።” ነበር ያሉኝ።
እሳቸው የሚያምኑት በገጠር ውስጥ ባማረ ግቢ ውስጥ የሚያምር ሕይወት መኖርን ነው። ምቾት ገጠርና ከተማ በማለት ሳይኾን በርትቶ በመሥራት የሚመጣ ነው። ግቢያቸውን እያዞሩ አስመለከቱኝ። ሲበዛ ያማረና በገጠር ውስጥ የተገኘ ቤተመንግሥት ነው የሚመስለው። በደጋጎቹ ቀዬ ደርሶ አፈር ስኾን እየተባለ የማይጎርስ፣ ስሞት እየተባለ የማይጠጣ የለምና ከመሶቡ እንጀራ እያወረዱ፣ ከገንቦው ማር እየቀዱ አቀማጠሉኝ። በዚያ በተዋበ ግቢ ውስጥ ያማረውን ሁሉ አደረጉልኝ። በዚያ ግቢ ውስጥ ቅሩ ቅሩ ያሰኛል። በአትክልቱ ግርጌ፣ በማሩ አጠገበ ኑሩ ያስብላል።
ደምቢያ እውነትም ማር ቀመስ፣ እውነትም አንጀት አርስ፣ እውነትም ድንቅ ሥፍራ። አመስግኛቸው በቀጭኗ መንገድ እያዘገምኩ ተመለስኩ። እግሬ ይጓዝ እንጂ ልቤ ግን ከመልካሙ ሥፍራ ግርጌ፣ ከደገኛው ሰው ጋር እንደተቀመጠ ነው። ደምቢያ ማር የሚቆረጥበት ደግነት የበዛበት ድንቅ ምድር። ብርቱ እጆች በገጠር ውስጥ ከተማ ይገነባሉ፣ ያማረ አምሳለ ቤተመንግሥት ግቢ ያበጃሉ። በዚያም ሥፍራ በደስታና በተድላ ይኖራሉ። ወርቄም በብርቱ እጆቻቸው መልካም ሥፍራ አበጅተው፣ በክብር እየኖሩ ነው። ያ ሥፍራ የአርሶ አደሮች ቤተመንግሥት ነው።
የምሥራቅ ደንቢያ ወረዳ የእንሥሳት እርባታና መኖ ልማት ቡድን መሪ ተስፋሁን ዓለሙ ደምቢያ የማር ምርት በስፋት የሚመረትበት ሥፍራ መኾኑን ነግረውኛል። የማር ምርቱን የፀረ ዓረም እና ሌሎች ችግሮች ቢፈታተኑትም ጥሩ የሚመረትበት ነውም ብለዋል። ማርን የደምቢያ መለያ ምርት ለማድረግ በንብ ማነብ ላይ የሚሠማሩ ፕሮጄክቶች ወደ አካባቢው እንዲገቡ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል። ሁሉም ሰው ቢያንስ ከባሕላዊ ቀፎ ወደ ሽግግር ቀፎ እንዲገባ የማድረግ ሥራ እየሠራን ነውም ብለዋል።
የማር ምርት ዋጋ እየጨመረ መሄድ አርሶ አደሮች ንብ የማነብ ተነሳሽነታቸው ከፍ እያለ እንዲሄድ እያደረገው መኾኑንም አንስተዋል። ፀረ ዓረም በንብ እርባታ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እየተሠራም ነው ብለዋል። ትል ንቦችን እንዳያጠቃ በባለሙያ ድጋፍ እየተሠራበት እንደሚገኝም ገልፀዋል።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!