ባሕር ዳር ለምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ እንግዶቿን ለመቀበል በዝግጅት ላይ መሆኗን ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡

0
73

ባሕር ዳር ለምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ እንግዶቿን ለመቀበል በዝግጅት ላይ መሆኗን ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡

ባሕር ዳር: ሰኔ 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የ2021 የምሥራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ (ሴካፋ) ውድድር በባሕር ዳር ይካሄዳል፡፡ ከ23 ዓመት በታች የቀጣናው ውድድር በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በባሕር ዳር ከተማ እንደሚካሄድ ከአሁን በፊት መገለጹ ይታወሳል፡፡ ከሰኔ 26 ጀምሮ የሚካሄደው የምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ውድድር አስተናጋጇ ኢትዮጵያን ጨምሮ 12 የቀጣናው እና ተጋባዥ ሀገራት እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

በተጋባዥነት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እንደምትሳተፍ ነው የሚጠበቀው፡፡

ለቀጣናው ውድድር አስተናጋጅነት የተመረጠችው ባሕር ዳር እንግዶቿን ለመቀበል ዝግጅት ላይ መሆኗን ከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ አብርሃም አሰፋ ለአሚኮ እንዳሉት እንግዶችን ለመቀበል ኮሚቴዎች ተዋቅረው እየተሠራ ነው፡፡ የበጎ ፈቃድ፣ የመዝናኛ፣ የሰላምና ጸጥታ፣ የመስተንግዶ እና ሌሎች ኮሚቴዎች ተዋቅረው እየተሠራ መሆኑንን ነው የተናገሩት፡፡

ባሕር ዳር ከተማ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማዘጋጀት ልምድ እና አቅም እንዳላት ገልጸዋል፡፡

ከተማዋ የጎብኚዎች መዳረሻ ናት ያሉት ኀላፊው ውድድሩ በኮሮናቫይረስ የተዳከመውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ከተማዋም ያገኘችውን እድል በአግባቡ ትጠቀምበታለች ነው ያሉት፡፡

ልክ እንደ ኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚዬር ሊግ ውድድር ሁሉ የሴካፋ ውድድርም ለከተማዋ ከፍ ያለ መነቃቃት እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡

እንግዶች የከተማዋን እና የኢትዮጵያን ገጽታ እንዲያውቁ የማድረግ ሥራ ይሠራል፤ ይሄን በማድረግ በኩል ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡

የነዋሪዎች የእንግዳ አቀባበል አስደሳች መሆኑን ያነሱት ኀላፊው እንደዚህ ቀደሙ ያለውን ጨዋነት እንዲያስቀጥሉና እንግዶች መልካም ትዝታ እንዲኖራቸው እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡

የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡

የባሕርዳር ከተማ አስተዳደርም ኢትዮጵያ የጣለችበትን አደራ እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡ ውድድሮች በተደጋጋሚ እንዲመጡና የከተማዋ የባሕልና ቱሪዝም እንቅስቃሴዎች እንዲጨምሩ የከተማዋ ወጣቶች የተሰጠውን መልካም እድል እንዲጠቀሙበትና አደራቸውን እንዲወጡም ነው የጠየቁት፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here