ባሕላዊ የእርቀ ሠላም ሥነ ስርዓት አካባቢው ሠላም እንዲሆን ማስቻሉን የዚገም ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

0
323

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 09/2012 ዓ.ም (አብመድ) ወይዘሮ አቡኔ የኔአባት የዚገም ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት ከቡና አጣጭ ጎርቤታቸው ጋር በመሬት ወሰን ጉዳይ በመካከላቸው አለመግባባት ይፈጠራል፡፡ ችግሩ አብረው ለዘመናት ክፉ ደጉን ያሳለፉ፣ ሲወጡ ሲገቡ የእግዜር ሰላምታ የሚለዋወጡ፣ በልጅ ፣ በከብት የማይተጣጡ ጎረቤታሞችን የሚያቃርን ሆነ፡፡ እርስ በርስ ለመነጋገር ሞከሩ መስማማት አልቻሉም፡፡ አለመግባባታቸው ወደ ግጭት እንዳያመራ ጉዳያቸውን ለሀገር ሽማግሌዎች ማወያየት ወደው አደረጉት፡፡ በዳይና ተበዳይ ሽማግሌ ፊት ቀርበው ቅሬታቸው በአግባቡ ተጠና፡፡ የማያሻማ ፍርድ ተሰጠ፡፡ ችግሩ ተፈታ፡፡ ይቅር ተባብለው የቀድሞ ሠላማዊ ሕይታቸው ቀጥሏል፡፡ ፍትሕን ፍለጋ ወደ መንግሥታዊ ተቋማት አልሄዱም፡፡ ጊዜ፣ ጉልበት እና ገንዘብ ሳያባክኑ በአካባቢያቸው ችግራቸውን ፈትተዋል፡፡

«በሽምግልና የተደረገው እርቀ ሠላም ከልብ ነው» ያሉት ወይዘሮ አቡኔ በፍርዱ መርካታቸውን ተናግረዋል፡፡ ለእርቀ ሠላም የተመረጡት ሽማግሌዎች ከሁሉም በላይ የሚታመኑ የፈረጠመ መንፈሣዊ ወኔ ያላቸው፣ የተበደለው ሰው ከቂሙ ነፃ እንዲወጣ ማድረግ የሚችሉ፣ አንደበተ ርቱዕ እና በሁለቱ ተሸማጋዮች ፍላጎት የተመረጡ መሆናቸዉን ወይዘሮ አቡኔ ተናግረዋል፡፡

ነገሮችን አድበስብሶ ለማስታረቅ አይሞክሩም፤ በሽምግልና ሂደቱም የበደለን ለመለየትና የበደሉን ዓይነት በሚገባ ለማወቅ ችግሩ በደንብ ይጣራል፤ የበደሉ ክብደት ይመዘናል፡፡ የበዳይ ጥፋት ተደጋጋሚነት ይታያል፡፡ በመጨረሻም በዳይ ድንጋይ ተሸክሞ ይቅርታ እንዲጠይቅ በማድረግ እና ተገቢውን ካሣ ክሶ በመካከላቸው ሠላም እንዲፈጠር እንደሚደረግ ወይዘሮ አቡኔ አጫውተውናል፡፡ «ባሕላዊ የእርቀ ሠላም ሥነ ስርዓት አገር ሠላም እንዲሆን አድርጓል» ብለዋል ወይዘሮ አቡኔ፡፡

ከመሬት ጋር የተያያዘ የይገባኛል ጥያቄ፣ ስርቆት እና አሉባልታ ወሬዎች በወረዳው ሰዎች ወደ ወንጀል እንዲገቡ የሚገፋፉ ጉዳዮች መሆናቸውን የሀገር ሽማግሌዎች ተናግረዋል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ግጭት በግለሰቦችም ይሁን በቡድን ደረጃ ይፈጠርና አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ (ኢኮኖሚያዊ) ቀዉስ ያስከትላል። በዚገም ወረዳ እነዚህን ግጭቶች በአካባቢዉ በሚገኙ ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች እና ተቋማት እየተፈቱ እንደሆነ ታዝበናል፡፡ ሽምግልና ግጭት ከመፈጠሩ በፊት እና ግጭት ከተፈጠረ በኋላ ግጭቱ ከመሠረቱ ተፈትቶ እንዲደርቅ ያደረጋል፡፡

በተለይም ግጭት ከተፈጠረ በኋላ የሚደረግ ባሕላዊ የሽምግልና ስርዓት ደም ማድረቅ ወይም ግጭቱ ድጋሚ እንዳይከሰት ማድረግ ነው፡፡ ይህን ተግባር የሚያከናውኑ ሽማግሌዎች ደግሞ በአካባቢው ቋንቋ «ደም አድራቂ ሽማግሌዎች» ይባላሉ፡፡ በእውነት፣ በእኩልነት፣ ለፍትሕ ይገዛሉ የተባሉ ሽማግሌዎች በሕዝብ ተመርጠው በዚህ ተግባር እንዲሳተፉ ይደረጋሉ፡፡ ለሽምግልና ብቁ ናቸው የተባሉ ግለሰቦችም በሃይማኖታዊ ሥነ ምግባራቸው የተመሠገኑ፣ በሰባዊነት እና በፍቅር የሚመሩ፣ ለሠላም የቆሙ፣ ተረት እና ምሳሌ አዋቂ፣ የማስረዳት እና የማሳመን ችሎታ ያላቸው መሆናቸውን በወረዳዋ በነበርን ቆይታ ማወቅ ችለናል፡፡

አቶ አሸብር አምሳሉ በዚገም ወረዳ የሚፈፀሙ ጎጂ ባሕላዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት የተቋቋመው የሠላም እና በጎ አድራጎት ማኅበር ሊቀ መንበር ናቸው፡፡ ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መካከል ደግሞ ደም መመለስ አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የበጎ አድራጎት ማኅበሩ በሚሠራው ሥራም የሀሰት ምስክርነት፣ ብቀላ እና ደም የመመላለስ ተግባር ቀንሰዋል›› ብለዋል አቶ አሸብር፡፡ በዋናነት ማኅበሩ ችግሮች ከመፈጠራችው በፊት ቤት ለቤት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

አንፃራዊ ሠላም እንዳለም የተናገሩት ሊቀ መንበሩ በበጎ አድራጎት ማኅበሩ 600 አባላት እና 14 ግጭት አስወጋጅ ኮሚቴዎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ ማኅበሩ በ2003 ዓ.ም ከብሔረሰብ አስተዳደሩ አስተዳደርና ፀጥታ መምሪያ ዕውቅና አግኝቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ ማኅበሩ የእርቀ ሠላም ሥራዎችን ከመሥራት ባለፈም ወላጅ አልባ ህፃናትንና አረጋውያንን ያግዛል፡፡

አቶ አስፈራው የኔአባት በዚገም ወረዳ የእርቀ ሠላም ሽማግሌ የኮሚቴ አባል ናቸው። በወረዳው ከዚህ በፊት ግድያ፣ ስርቆት እና ብቅላ በስፋት ይፈጸም እንደነበር በማመልከት ችግሩን ለመቀነስ 60 ሽማግሌዎች ማኅበሩን በመመሥረት የተጣሉ ሰዎችን ማስማማት መጀመራቸውን ነ