“ባለፉት 9 ወራት ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል” የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር

142

ባሕር ዳር: ግንቦት 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ሚኒስቴሩ ከ3 ሚሊየን በላይ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር አቅዶ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን በአርባምንጭ ከተማ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸሙን በገመገመበት ወቅት ገልጿል፡፡

በአፈጻጸሙ ላይ በአገልግሎት ዘርፍ ለ1 ሚሊየን ዜጎች የሥራ እድል እንደተፈጠረ ተገልጿል። በግብርና ለ962 ሺህ እንዲሁም በኢንዱስትሪ ዘርፉ ለ493 ሺህ ዜጎች የስራ እድል እንደተፈጠረ ተጠቁሟል፡፡

በሥራ እድል ፈጠራው የግብርና እና የኢንዱስትሪ ዘርፎች ቀዳሚ እንዲኾኑ ለማድረግ መሥራት እንደሚገባ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገልጸዋል
በዘጠኝ ወራት ውስጥ በውጭ ሀገራት ስምሪትም ለ59 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል እንደተፈጠረ ነው የተገለጸው፡፡

ሚኒስቴሩ ከውጭ ሀገራት ስምሪት ጋር በተያያዘ የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ ሲሠራ እንደቆየም ተገልጿል። በማንዋል የነበሩ የውጭ ሀገር ስምሪት ሥራዎችን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ዜጎችን ሲያስተጎጉሉ የነበሩ ችግሮችን መቅረፍ ተችሏልም ተብሏል፡፡

ባለፉት ወራት በቴክኒክና ሙያ ዘርፎች በመደበኛ እና አጫጭር ሥልጠናዎች ሙያተኞችን የማፍራት ሥራ መከናወኑን ፋናቢሲ ዘግቧል።

በግምገማው በሥራ እድል ፈጠራ፣ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ እና በውጭ ሀገራት ስምሪት የተገኙ ስኬቶችና መሻሻል ያሉባቸው ጉዳዮች መለየታቸውም ተነስቷል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!