ባለፉት 9 ወራት ከወጭ ንግድ 2 ነጥብ 45 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

0
63

ባለፉት 9 ወራት ከወጭ ንግድ 2 ነጥብ 45 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 06/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያለፉት 9 ወራት የወጭ ንግድ አፈፃፀም
ከሚመለከታቸው ኀላፊዎች ጋር ገምግሟል፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል መንግሥት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ድርሻው
የተሻለ እንዲሆን ለማድረግ ለሲሚንቶ አምራች ኢንዱስትሪዎች 85 ሚሊዮን ዶላር ለሌሎች አምራች ኢንዱስትሪዎች ደግሞ 40
ሚሊዮን ዶላር በልዩ ሁኔታ መፍቀዱን ገልጸዋል፡፡ ኢንዱሰትሪዎች ያለባቸውን የፋብሪካ የመለዋወጫ ችግር ቀርፈው በሙሉ
አቅማቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አምራቾች የተፈቀደላቸውን የውጭ ምንዛሬ ለሚፈለገው ዓላማ ብቻ በማዋል የሚጠበቅባቸውን ሀገራዊ የኢኮኖሚ የዕድገት
ድርሻ እንዲወጡ ለማድረግ እየተሠራ ያለው የድጋፍ፣ክትትልና ቁጥጥር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪው የምርት መዳረሻ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መሻሻል እያሳየ መሆኑ መልካም አጋጣሚ በመሆኑ
በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡
የዓለም የምርት የመሸጫ ዋጋ ከእጥፍ በላይ የጨመረ መሆኑን የጠቀሱት አቶ መላኩ ስኳርን ለምርት ግብዓትነት የሚጠቀሙ
አምራቾች በፍራንኮ ቫሉታ ከውጭ አስገብተው እንዲጠቀሙ የተፈቀደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የወጭ ንግድ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ፈታኝ በሆኑ ዓለምአቀፋዊና ሀገራዊ ሁኔታዎች ውስጥም ሆነን
በወጭ ንግድ ገቢው እየተመዘገበ ያለው ስኬት አበረታች በመሆኑ ችግሮችን ለይተን የመፍትሔ አቅጣጫ በማስቀመጥ የበለጠ
ለውጥ ለማስመዝገብ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
የአግሮ ፕሮሰሲንግና ፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገ/እየሱስ በበኩላቸው የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የወጭ
ንግድ ገቢ መቀነስ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የመዳረሻ ሀገራት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመዳከሙ የተፈጠረ መሆኑን
ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የምርቶችን መዳረሻ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ መነቃቃትና የሀገሪቱን ምርት ለመግዛት ፍላጎት እያሳዩ በመሆኑ ለአምራች
ዘርፉ አስፈላጊው የውጭ ምንዛሬ ተፈቅዶለት የሚያስፈልገውን በማሟላት በሙሉ አቅሙ ወደ ምርት እንዲገባ እየተሠራ መሆኑን
አመላክተዋል፡፡ የአምራች ዘርፍ አካላት የተፈቀደላቸውን የውጭ ምንዛሬ ተጠቅመው ምን ያህል ገቢ እንዳስገኙና ለምን አይነት
አገልግሎት እንደተጠቀሙ ለማወቅ ጥናት እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በግምገማው በመጋቢት ወር ከወጭ ንግድ 366 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 353 ሚሊየን ዶላር በማግኘት የእቅዱን 96
ነጥብ 5 በመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡ አፈጻጸሙም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር የ26 በመቶ ብልጫ አስመስግቧል፡፡
ባለፋት 9 ወራትም 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 2 ነጥብ 45 ቢሊየን ገቢ ወይም የእቅዱን 84 በመቶ ማሳካት
እንደተቻለ መገለጹን ከንግድና ኢንዱሰትሪ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here