ባሕር ዳር: ግንቦት 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የብድር አቅርቦት አለመመቻቸት በሥራቸው ላይ ፈተና እንደኾነባቸው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶች ማንሳታቸውን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር የካልሚ የዘይት ፋብሪካ እና የገንዳውኃ ጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ ያነሱትን የብድር አቅርቦት አለመመቻቸት ጥያቄን ገልጸን ዘገባ መሥራታችን ይታወሳል። ይህንን አስመልክቶ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ባለሃብቶች የብድር ተጠቃሚ እንዲኾኑ ጥረት እያደረገ እንደኾነ ገልጿል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ይኸነው ዓለም ቢሮው ባለሃብቶች ብድር እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ዋነኛ ተግባሩ እንደኾነ ነው ያስረዱት፡፡
በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት በክልሉ የሚገኙ ባለሃብቶች ከብድር ጋር ተያይዞ ያጋጠማቸውን ችግር ለመፍታት ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል።
በ2015 ዓ.ም ዘጠን ወራት መስፈርቱን ላሟሉና ያቀረቡት ፕሮጀክት አዋጭ ኾኖ ለተገኙት ፦
👉 ለ200 ባለሃብቶች 2 ነጥብ 16 ቢሊዮን ብር ማሽን ተገዝቶ እንዲቀርብ ተደርጓል።
👉 ለ154 ባለሃብቶች ፕሮጀክታቸውን ብቻ በመያዣነት ተጠቅመው 12 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የብድር ተጠቃሚ እንዲኾኑ መደረጉን ገልጸዋል።
👉 ለ260 ባለሃብቶች ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ የሥራ ማስኬጃ ብድር እንዲያገኙ ተደርጓል።
አቶ ይኸነው ባለሃብቶች ከዚህ በፊት የወሰዱትን ብድር ካልመለሱ ባንኮች ዳግም ብድር መስጠት እንደማይችሉም ነው ያስገነዘቡት።
በዚህ መሠረት የካልሚ የዘይት ፋብሪካ በብድር ምክንያት ወደ ሥራ መግባት እንዳልቻለ የተነሳው ቅሬታ ተገቢ አለመኾኑን ገልጸው ብድር የተከለከለው ከዚህ በፊት ባቀረበው ፕሮጀክት የተበደረውን 90 ሚሊዮን ብር ባለመመለሱ ምክንያት እንደኾነ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ የገንዳውኃ ጥጥ መዳመጫ ፋብሪካም 80 ሚሊዮን ብር የባንክ ብድር ባለመመለሱ ዳግም የብድር ተጠቃሚ አለመኾኑን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ባለሃብቶች ማሟላት የሚገባቸውን የብድር መስፈርት ባለማሟላት እና በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ማሽኖችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የመጓተት ነገሮች መኖራቸውን የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው አብራርተዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!