ባለፈው በጀት ዓመት 138 ሚሊዮን ብር ወደ መንግሥት ካዝና ገቢ መደረጉ ተገለጸ፡፡

0
140

ባሕር ዳር፡ መስከረም 9/2012 ዓ.ም (አብመድ) በ2011 በጀት ዓመት በሙስና ወንጀሎች ሀብትን በማስመለስ እና በማስከበር ዙሪያ 138 ሚሊዮን ብር ወደ መንግሥት ካዝና ገቢ መደረጉን በኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተረፈ አሰፋ ገለጹ፡፡

ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን በመታገልና ያለአግባብ በመንግሥት ላይ ኪሳራ ባደረሱ አካላት ዐቃቤ ሕች ምርመራ በማድረግ ክስ መመሥረታቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ለዚሁ ያግዝ ዘንድ ለዐቃቤ ሕጎች የተለያዩ የክህሎት ማጎልበቻ ስልጠናዎች መሰጠቱንም ነው የገለጹት፡፡

የቀድሞው የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በአዋጅ ቁጥር 1097/2011 ዓ.ም ወደ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መቀየሩን ተከትሎ ከተጨመሩለት ተግባርና ኃላፊነቶች መካከል ምርመራን መምራትና ማስተባበር ዋነኛው መሆኑን ጠቁመው በዚህም በአገሪቱ ላይ የተፈጸሙ ከባድ ወንጀሎች ላይ ምርመራ በመምራትና በማስተባበር በወንጀሉ ላይ የተሳተፉ አካላትን በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረጉ አስረድተዋል፡፡

ለአብነትም በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ)፣ በዉኃ ሥራዎችና ኮንስትራክሽንና በመንግሥት ግዥ ኤጀንሲ ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች ምርመራ ተደርጎባቸዉ ክስ መመሥረቱን አውስተዋል፡፡

ዳይሬክቶሬቱ የወንጀሉን ዉስብስብት በመረዳትና ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት ያመቺ ዘንድ በሙስና ወንጀል የተገኙትን ሀብቶች የሚያስመልስና የሚያስወርስ እንዲሁም በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በፍትሕ አስተዳደር ዘርፍ የሚሠሩ ማስተባበሪያዎችን በማደራጀት በበጀት ዓመቱ በሙስና ወንጀሎች ዙሪያ ስኬታማ ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችል አደረጃጀት መፍጠሩን አቶ ተረፈ ገልፀዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ከለዉጡ ማግስት የሰማዉን ብስራት ቶሎ ቶሎ ማወቅ በመፈለጉ የሙስና ትግሉ ተዳክሟል የሚሉ ትችቶችን ሲያነሳ ይስተዋላል ተብሎ ለተነሳዉ ጥያቄ የሙስና ትግሉ በተጠናከረ ሁኔታ መቀጠሉንና ምርመራዎች ጊዜን መሠረት አድርገዉ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን የማሰባሰብ ሥራ የሚከናወን ከመሆኑም በተጨማሪ በትኩረትና በጥንቃቄ መመራት ያለበት በመሆኑ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ የሚሆኑ መረጃዎች የመዘግየታቸዉ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በ2012 በጀት ዓመትም በሀብት ማስከበርና ማስመለስ እንዲሁም ማስወረስ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
የሙስና ወንጀል ዉስብስብ በመሆኑ የፍትሕ አካላት ጉዳይ ብቻ ሊሆን እንደማይገባው ያመለከቱት አቶ ተረፈ ‹‹የኅብረተሰቡን ሰፊ ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ወንጀልን በማጋለጥ የራሱን ሚና መጫዎት ይገባዋል›› ብለዋል፡፡

ምንጭ፡- የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ