ቡና ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር ለሕልውና ዘመቻው 1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።

0
50

ቡና ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር ለሕልውና ዘመቻው 1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 24/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር ችግር በገጠማት ወቅት ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች የሀገርን ሕልውና የማስጠበቅ ኀላፊነት አለባቸው። ቡና ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር ለሕልውና ዘመቻው ያደረገው ድጋፍም በዚህ መነሻነት የተደረገ መኾኑ ተመላክቷል። የአክሲዮን ማኅበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳኛቸው መሐሪ ሕልውናን የማስጠበቅ ኀላፊነት ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም፤ መንግሥትም ብቻውን ሊወጣው አይችልም ነው ያሉት።

ድጋፉ ለሀገራዊ ጥሪው ምላሽ ለመስጠት መነሻ እንጂ በቂ አይደለም ብለዋል። በቀጣይም አክሲዮን ማኅበሩ ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያስታወቁት።

አንዱ ለሕልውና ሲፋለም ሌላው ቆሞ ተመልካች መሆን የለበትም ያሉት አቶ ዳኛቸው ሌሎች የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አቅሙ በፈቀደ መጠን በዘመቻው መሳተፍ አለባቸው ብለዋል።

የአማራ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ኀላፊና የሕልውና ዘመቻው ሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ጥላሁን መሐሪ የክልሉ መንግሥት ያቀረበውን ድጋፍ ጥሪ ተከትሎ በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሕይወት መስዋእትነት ከመክፈል ጀምሮ በተለያየ መልኩ ድጋፍ እያደረጉ ነው ብለዋል።

ቡና ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበርም ለክልሉ መንግሥት ጥሪ ምላሽ ሰጥቷል ነው ያሉት። የሕልውና ዘመቻው እስከሚጠናቀቅ ቡና ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነትም ተናግረዋል።

የአክሲዮን ማኅበሩ እህት ድርጅት የሆነው ቡና ባንክ በባለፈው የሕግ ማስከበር ዘመቻ 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል። የቡና ባንክ ሠራተኞችም ድጋፍ እንዲያደርጉ በቀረበላቸው ጥሪ መሠረት ጥሩ ምላሽ እየሰጡ ነው ብለዋል።

የሚሰበሰበው ሀብት ለሕልውና ዘመቻው ሥራ ብቻ እንደሚውል ያስገነዘቡት ዶክተር ጥላሁን ዘመቻው እስኪጠናቀቅ ሁሉም አካል ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here