በ6ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ፋሲል ከነማን ከባሕር ዳር ከነማ ያገናኛል፡፡

0
339

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 22/2012ዓ.ም (አብመድ) በኢትዮጵያ የወንዶች ፕሪሚዬር ሊግ አማራ ክልልን የሚወክሉት ፋሲል ከነማና ባሕር ዳር ከነማ በ6ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታቸውን ጎንደር ላይ ይናኛሉ፡፡

በድንቅ የአደጋፍ ሥርዓት የሚታወቁት ፋሲል ከነማና ባሕር ዳር ከነማ እግር ኳስ ቡድኖች በ6ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታ ጎንደር ላይ የሚያደርጉትን ጨዋታ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በቀጥታ ያስላፈዋል፡፡ እስካሁን በተደረጉ 5 የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ከሜዳቸው ውጭ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት የተሳናቸው ሁለቱ ቡድኖች በስድስተኛ ሳምንት እርስ በርስ ሊገናኙ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ በ5ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ፋሲል ከነማ እስከ 90ኛው ደቂቃ ድረስ 3 ለ1 በሆነ ውጤት ሲመራ ቆይቱ በተሰጠው የጭማሪ ደቂቃ 2 ግብ ተቆጥሮበት በአቻ ውጤት እንዲያጠናቅቅ ተገድዷል፡፡ ዓፄዎቹ በሜዳቸው ያላቸውን ያለመሸነፍ ጉዞ ለማስቀጠል የጣና ሞገዶቹን በሜዳቸው ዓፄ ፋሲለድስ ስታዲዬም ይጋብዛሉ፡፡ ዓፄዎቹ በሜዳቸው ያደረጓቸውን ሁለት ጨዋታዎች በሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡

ከሜዳው ውጭ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት የተሳነው ባሕር ዳር ከነማም በ5ኛ ሳምንት ከሜዳው ውጭ ሀድያ ሆሳዕናን ገጥሞ በአቻ ውጤት ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ ባሕር ዳር ከነማ በሜዳው ያደረጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች በድል ተወጥቷል፡፡ ፋሲል ከነማ በሜዳው ያለመሸነፍ ጉዞውን ለማስቀጠል ባሕር ዳር ከነማ ደግሞ በውድድር ዓመቱ ከሜዳው ውጭ የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ ለማስመዝገብ ይጫወታሉ፡፡

ጨዋታው በርካታ ደጋፊዎች በስታዲዬም የሚገኙበት መሆን በአስደናቂ የሜዳ ላይ ዝማሬ መታጀብ ከወዲሁ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡ ፋሲል ከነማና ባሕር ዳር ከነማ በእኩል 8 ነጠብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 4ኛና 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ጨዋታው የፊታችን ቅዳሜ ታኅሣሥ 25 ቀን 2012ዓ.ም ጎንደር ዓፄ ፋሲለደስ ስታዲዬም ላይ ይደረጋል፡፡ እርስ በርስ በሚገናኙበት የ6ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የሚያሸንፈው ነጥቡን በሦስት ከፍ ያደርጋል፡፡ አቻ የሚለያዩ ከሆነ ደግሞ በተመሳሳይ ነጥብ 7ኛ ሳምንት ጨዋታቸውን ይጠብቃሉ፡፡

‹የወንድማማቾች ደርቢ› እየተባለ የሚጠራው ይህ ጨዋታ እሑድ ታህሳስ 26 ቀን 2012ዓ.ም እንዲደረግ ቀጠሮ ተይዞለት የቆዬ ቢሆንም ፋሲል ከነማ ‹‹ካለብኝ የጨዋታ መደራረብ አ ንጻርቀኑ ወደ ቅዳሜ ይቀየርልኝ›› በማለት ለፌዴሬሽኑ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ቀኑ ወደ ቅዳሜ ታኅሣሥ 25 ቀን መቀየሩን የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን ሥራ አስኪያጅ አብዮት ብርሃኑ ለአብመድ ገልጸዋል፡፡

ፋሲል ከነማ ታኃሳስ 29 ቀን 2012ዓ.ም 7ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታውን ከሜዳው ውጭ ከወላይታ ዲቻ ጋር በሶዶ ስታዲዬም ያጫወታል፡፡ ይህ ደግሞ ፋሲል ከነማ እሑድ ጎንደር ላይ ተጫውቶ ወደስፍራው ለመሄድ በቂ ጊዜ ስለሚያስፈልገው ነው ጥያቄውን ያቀረበው፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ ወላይታ ዲቻ የሚደረገው ጉዞ በመኪና ስለሚሆን የተጫዋቾችን ድካምና የጊዜ እጥረት በማዬት አንድ ቀን ሽግሽግ እንዲደረግለት ፌዴሬሽኑን በጠየቀው መሠረት ነው የተፈቀደለት፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዡን ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና መቀሌ 70 አንድርታ በእኩል 10 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሲመሩት ሲዳማ ቡና በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ስሁል ሽረ ድሬዳዋ ከነማና ሀድያ ሆሳዕና ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ፡፡

በታርቆ ክንዴ