ባሕር ዳር: ግንቦት 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በ2015/16 የሰብል ልማት የምርት ዘመን ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ አቅዶ እየሠራ መኾኑን የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታውቋል።
በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የደዋ ጨፋ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የ2015/16 የምርት ዘመን የመኸር ሰብል ልማት ንቅናቄ መድረክ ከግብርና ቤተሰቦችና ባለድርሻ አካላት ጋር አካሄዷል።
የደዋ ጨፋ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አብዱ መሀመድ አሚን ባስተላለፉት መልእክት በወረዳው 16 ሺህ 5 መቶ ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን ከ480 ሺህ በላይ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ወረዳው አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ አዲሱ ቡላ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ ገብተናል ነው ያሉት።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አህመድ አሊ የተያዘው እቅድ እንዲሳካ ምርጥ ዘርን በመጠቀምና በኩታ ገጠም በማረስ ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
የልማት ሥራዎችን መከወን የምንችለው የብሔረሰብ አሥተዳደሩን ሰላም ሲረጋገጥ ነው ያሉት አሥተዳዳሪው ሰላምን ለማረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሂም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!