ደብረማርቆስ:የካቲት 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ማኀበሩ በተያዘው በጀት ዓመት ከአባላት ሊሰበስብ ካቀደው 419 ሚሊዮን ብር ውስጥ በግማሽ ዓመቱ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ ለማኀበረሰቡ ልማት እያዋለ መኾኑን አስታውቋል::
ተማሪ ሰናይት ሞላ በባሶ ሊበን ወረዳ የደን ቀበሌ ነዋሪ ናት። ታዳጊዋ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ብትኾንም በአካባቢው ትምህርት ቤት ባለመኖሩ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቷን ለመከታተል ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ለሰዓታት መጓዝ ግድ ኾኖብኛል ትላለች ።

ትምህርቷን ለመቀጠል ውጣ ውረድን እየታገለች የምትገኘው ታዳጊዋ አማራ ልማት ማኀበር በደን ቀበሌ የገነባው 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለቀየዋ ታዳጊዎች ተስፋን ይዞ መጥቷል ፡፡ ትምህርትን ፍለጋ ሰዓታትን መጓዝም ማብቂያው ጊዜ የደረሰ ይመስላል ብላለች።
የደን ቀበሌ ነዋሪዎችም ልጆቻቸው የ2ኛ ደረጃ ትምህርትን ፍለጋ የሚያደርጉትን የረዥም መንገድ ጉዞ በማስቀረት በቅርበት የመማር ዕድል እንዲያገኙ ለትምህርት ቤት ግንባታ መሬታቸውን ከመልቀቅ ጀምሮ ልማት ማኀበሩ የሚያከናውናቸውን የልማት ተግባራት በገንዘብ እና በጉልበት እየደገፉ መኾናቸውን ነግረውናል፡፡
በቀበሌያቸው የተገነባው 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሥራ እስኪጀምር ጓጉተዋል፡፡ የልጆቻቸው እንግልት የሚያበቃበትን ጊዜም ናፍቀዋል። የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ አቶ ደመላሽ ታደሰ ለባሶ ሊበን ወረዳ የደን ቀበሌ ነዋሪዎች 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ ሥራ ለመጀመር የሚያስችሉ ቅድመ ኹኔታዎች ሲሟሉ ማስተማር እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡

የአማራ ልማት ማኀበር አልማ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ዘላለም አንዳርጌ ልማት ማኀበሩ የማኀበረሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በተያዘው በጀት ዓመት 14 የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ ደግሞ 86 የልማት ፕሮጀክቶችን እያከናወነ መኾኑንም ተናግረዋል።
አቶ ዘላለም በዞኑ አማራ ልማት ማኀበር ከ600 ሺህ በላይ አባላት ሲኖሩት በተያዘው ዓመትም 419 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ዓቅዶ በግማሽ ዓመቱ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ከአባላቱ በመሰብሰብ ለማኀበረሰብ ልማት እያዋለ ነው ብለዋል።
የአማራ ልማት ማኀበር አልማ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ሞገስ ልማት ማኀበሩ በክልሉ በተለይም በትምህርትና በጤና ዘርፍ የመንግሥትን የልማት ክፍተት በመሙላት ማኀበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም አልማ ከሕዝቡ በሚሰበሰብ ሐብት በሃምሌ ወር ብቻ ከ200 በላይ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለሕዝቡ ሲያስረክብ 1000 የልማት ፕሮጀክቶችን ደግሞ እያከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል። ሕዝቡ በልማት ማኀበሩ አባል በመኾን የራሱን ችግር በራሱ ለመፍታት እያሳየ ያለው ተነሳሽነትም ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የአማራ ልማት ማኅበር ከአራት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ አባላትን በመያዝ የክልሉን ሕዝብ የልማት ፍላጎት ለማሟላት እየሰራ ሲኾን እስከ ሚቀጥለው በጀት ዓመት የአባላቱን ቁጥር ወደ 7 ሚሊዮን ለማሳደግ እየሰራ መኾኑንም ከልማት ማኀበሩ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
ዘጋቢ፡- ዘላለም አስፋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!