ባሕር ዳር: ግንቦት 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በ2015 በጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ 541 የመንገድ፣ የድልድይ እና ተጓዳኝ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሔደ ነው መኾኑን የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ገልጿል። ከሚገነቡት ፕሮጀክቶች ውስጥ 500 ያህሉ በበጀት ዓመቱ እንደሚጠናቀቁ ቢሮው ገልጿል፡፡
የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ የሕዝብ ግኝኙነት ኀላፊ በትግሉ ተስፋሁን በሰጡት ማብራሪያ በአማራ ክልል እስከ አሁን ያለው አጠቃላይ የመንገድ ሽፋን ከ30 ሺህ 700 በላይ ኪሎ ሜትር ደርሷል፡፡ ይሁን እንጅ ክልሉ ካለው ቆዳ ሥፋትና የሕዝብ ብዛት አኳያ ብዙ ሥራ ይጠይቃል ብለዋል፡፡ በዚህም በ2022 የክልሉን መንገድ ሽፋን ከ51 ሺህ 600 በላይ ኪሎ ሜትር ለማድረስ እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡
ቢሮው በ2015 በጀት ዓመት 541 መንገድ፣ ድልድይ እና ተያያዥ ፕሮጀክቶችን እየገነባ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡ ለግንባታው ደግሞ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት ተመድቦላቸዋል፡፡
በግንባታ ላይ ከሚመገኙት ውስጥ ደግሞ፡-
👉 154 ፕሮጀክቶች በክልሉ መንግሥት
👉 200 ፕሮጀክቶች በፌደራል መንገድ ፈንድ
👉 187 ፕሮጀክቶች ደግሞ በማኅብረተሰቡ ተሳትፎ በመገንባት ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡
በመገንባት ላይ ከሚገኙት ውስጥ 500 ፕሮጀክቶች በዚህ በጀት ዓመት እንደሚጠናቀቁ ኀላፊው ገልጸዋል፡፡
አጠቃላይ በፕሮጀክቶች ግንባታ ከ710 በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች በቋሚነት፣ ከ10 ሺህ በላይ ወጣቶች ደግሞ በጊዜያዊነት የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው ኀላፊው ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!