በ2013/14 የመኸር እርሻ ከ6 መቶ ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቅባት እህል በዘር ለመሸፈን እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

266

በ2013/14 የመኸር እርሻ ከ6 መቶ ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቅባት እህል በዘር ለመሸፈን እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 23/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሠብል ልማት ባለሙያዋ ወይዘሮ እንዬ አሠፋ በመኸር እርሻው 661 ሺህ 262 ሄክታር መሬት በቅባት ሠብሎች በዘር በመሸፈን 7 ሚሊዮን 547 ሺህ 451 ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ነግረውናል፡፡
• አኩሪ አተር 143 ሺህ 372 ሄክታር
• ኑግ 37 ሺህ 819 ሄክታር
• ተልባ 12 ሺህ 296 ሄክታር
• ለውዝ 18 ሺህ 967 ሄክታር
• ሱፍ 20 ሺህ 590 ሄክታር
• ጎመን ዘር 421 ሄክታር
• ሠሊጥ 427 ሺህ 797 ሄክታር መሬት በድምሩ 661 ሺህ 262 ሄክታር መሬት በቅባት እህሎች በዘር ይሸፈናል ብለዋል፡፡

በዘር ከሚሸፈነው መሬት ውስጥ 9 ሺህ 9 ሄክታር መሬት የባለሀብቶች ሲሆን ቀሪው 652 ሺህ 253 ሄክታር መሬት የአርሶ አደሮች ማሳ መኾኑን ባለሙያዋ ነግረውናል፡፡ ባለሙያዋ እንዳሉት የዚህ ዓመት እቅድ ካኹን በፊት በክልሉ ሦስት በመቶ የነበረውን የማሳ ሽፋን ወደ 14 በመቶ ያሳድገዋል፡፡

እቅዱ የቅባት እህሎችን አምርቶ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ለማዋል የተያዘውን እቅድ ለማሳካት እንደሚረዳም ተናግረዋል፡፡ ወይዘሮ እንዬ ሠሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ሱፍ እና ለውዝ በአራት ዞኖችና በ17 ወረዳዎች በዋናነት የሚለሙ ሠብሎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ እንደ ተልባ፣ ጎመን ዘር እና ኑግ የመሳሰሉ ሠብሎች ደግሞ በሌሎች አካባቢዎች ይለማሉ ብለዋል፡፡

ባለሙያዋ እንደተናገሩት በሥራው ላይ ከሦስት ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች የሚሳተፉ ሲሆን 109 ሺህ 619 አርሶ አደሮች በአኩሪ አተር ማምረት ላይ ተሳታፊ ናቸው፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ለሥራው ትኩረት በመሥጠት 24 ኩንታል በሄክታር የነበረውን የአኩሪ አተር ምርታማነትን ወደ 28 ኩንታል ለማሳደግ እየሠራ መሆኑንም ነግረውናል፡፡ ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ ለአርሶ አደሮች፣ ለቀበሌ እና ለወረዳ ባለሙያዎች ሥልጠና ተሠጥቷል ነው ያሉት፡፡ ወይዘሮ እንዬ አርሶ አደሮች ማሳቸውን ደጋግመው በማረሥ እና በአግባቡ በማለስለስ እንዲዘሩ፣ የተዘሩ ሠብሎችንም የአረም እና የተባይ ቁጥጥር በማድረግ ለተሻለ ውጤት መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

በ2013/14 የመኸር እርሻ ከአራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን 131 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m