“በ175 ጥቆማዎች ላይ ምርመራ በማድረግ በሰማንያ አንዱ ላይ የክስ መዝገብ አደራጅተናል።” ብሔራዊ የጸረ-ሙስና አስተባባሪ ኮሚቴ

46
ባሕርዳር: የካቲት 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የብሔራዊ የጸረ-ሙስና አስተባባሪ ኮሚቴ በ175 ጥቆማዎች ላይ ምርመራ በማድረግ በሰማንያ አንዱ ላይ የክስ መዝገብ ማደራጀቱን የኮሚቴው ሰብሳቢና የብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
የብሔራዊና የክልል የጸረ-ሙስና ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና አባላት የጋራ የአፈጻጸም ግምገማ መድረክ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
የኮሚቴው ሰብሳቢና የብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ኮሚቴው ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ 759 ጥቆማዎች ደርሰውታል።
ይህንንም ተከትሎ ኮሚቴው በ175ቱ ጥቆማዎች ላይ ምርመራ ማድረጉን ጠቅሰው በ81 ላይ የክስ መዝገብ መደራጀቱን ነው የገለጹት።
የክስ መዝገብ በተደራጀባቸው መዝገቦች ውስጥም 640 ተጠርጣሪዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
እስከ አሁን በተደረጉ የማጣራት ሥራዎችም 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ግምት ባላቸው የመንግሥትና የሕዝብ ኃብት ላይ ጉዳት መድረሱ ተረጋግጧል ብለዋል።
ሙስና በሀገር ደረጃ ትልቅ ፈተና እየኾነ መጥቷል ያሉት የኮሚቴው ሰብሳቢ ሙስና የሀገርን ዕድገት የሚገታ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን የሚያባብስ እኩይ ድርጊት መኾኑን ገልጸዋል።
በመኾኑም ኮሚቴው የጀመረውን የጸረ-ሙስና ትግል አጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ብሔራዊ ኮሚቴው ይህን ለሀገር ፈተና የኾነውን ሙስና ለመከላከልና ለሀገር ሥጋት ወደ ማይኾንበት ደረጃ ለማድረስ ታስቦ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ህዳር ወር መቋቋሙ ይታወሳል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!